
26/09/2025
ራሳችሁን በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ብታገኙትስ?
የኬንያ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት፣ ዜጎችን በሞስኮ ሥራ እናስቀጥራችኋለን በሚል ማማለያ፣ በሩሲያ የጦር ግንባር ውስጥ የሚዶል ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ሰንሰለትን ማፈራረሱን አስታወቀ፡፡
ቡድኑ፤ በከፍተኛ ደሞዝ ሥራ እናስቀጥራችኋለን በሚል ሃሰተኛ ተስፋ በማጭበርበር፣ ለቪዛ፣ ለጉዞና ለማረፊያ ከ12ሺ እስከ 17ሺ ዶላር የሚደርስ ክፍያ እንደሚያስከፍል ታውቋል፡፡
መርማሪ ፖሊሶች ባደረጉት የክትትል ዘመቻ 21 ኬንያውያንን መታደጋቸው የተዘገበ ሲሆን፤ የድርጊቱ አስተባባሪ ነው የተባለ አንድ ተጠርጣሪም በቁጥጥር ስር መዋሉ ተጠቁሟል፡፡
መርማሪዎቹ የጉዞ ሰነዶችን፣ የሥራ ቅጥር ደብዳቤዎችንና ከሩሲያ ሁለት የቅጥር ኩባንያዎች ጋር የተገናኙ ውሎችን ማግኘት መቻላቸው ተዘግቧል፡፡
የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ባለሥልጣናቱ፣ በኬንያ ያሉ ገንዘብና ሥልጣን ያላቸው ግለሰቦች፣ ለቡድኑ ከለላ ሰጥተውት ቆይተው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡
የእንደዚህ ዓይነቱ የወንጀል ድርጊት ሰለባ ከነበሩት መካከል ኢቫንስ የተባለው ኬንያዊ ተጠቃሽ ሲሆን፤ በዩክሬን የጦር ምርኮኛ መሆኑን የሚገልጽ ቪዲዮ ላይ ከታየ በኋላ ታሪኩ በሰፊው ተሰራጭቷል። ለአትሌቲክስ ውድድር ነው ተብሎ ወደ ሩሲያ መጓዙን የሚገልጸው ኬንያዊው፤ በዩክሬን ሰራዊት ከመያዙ በፊት ለሩሲያ ጦር እንዲዋጋ መገደዱን ተናግሯል።
***
ወገኖቼ፤ ከዚህ ዘገባ የምንማረው ትልቅ ቁምነገር አለ፡፡ ይሄ ነገር በጎረቤት ኬንያ ከተከሰተ በኛም አገር የማይከሰትበት ወይም የማይሞከርበት ምክንያት የለምና ጥንቃቄ ማድረግ መልካም ነው፡፡ እስካሁን ላለመደረጉም በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ህጋዊና ህጋዊነትን ብቻ እንምረጥ ለማለት ነው፡፡