25/06/2025
በኢትዮጵያ 70 የፌዴራል ተቋማት እና ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶቻቸው መመሪያን ሳይከተሉ ከ404 ሚሊዮን በላይ በሆነ ብር ግዢ መፈፀማቸውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ።
መመሪያን ሳይከተሉ ግዢ ከፈፀሙ ተቋማት መካከል የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፣ አርሲ ዩኒቨርሲቲ፣ እና በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር-2 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እንደሚገኙ ተገልጿል።
ይህ የተገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 39ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባቀረቡት የፌዴራል መስሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ነው።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በ70 የፌዴራል ተቋማት እና በ7 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቻቸው ከ404 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ በሆነ ብር የመንግሥትን የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዢ ተፈጽሞ ተገኝቷል ብለዋል።
በተጨማሪም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ያለፍቃድ የቀን ሠራተኞችን ለቋሚ የሥራ ቅጥር መደቦች በመቅጠር ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸማቸው ተገልጿል፡፡
በዚህም ጅማ ዩኒቨርሲቲ 25,310,211 ብር፣ አምቦ ዩኒቨርሲቲ 10,938,834 ብር፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ 7,888,374 ብር፣ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ 5,170,600 ብርና ዲላ ዩኒቨርሲቲ 4,414,974 ብር ክፍያ መፈጸማቸው ተጠቅሷል፡፡
የምክር ቤት አባላት የሀብት ብክነትን መቆጣጠርና ተጠያቂነት ማስፈን ላይ ዋና ኦዲተር በትኩረት እንዲሰራ ያሳሰቡ ሲሆን፤ የኦዲት ክፍተት የተገኘባቸውና ሀብት ያባከኑ ተቋማትና የሥራ ኃላፊዎች ተጠያቂ በማድረግ ረገድ ያሉ ውስንነቶች መቀረፍ እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን ከምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት መሰረት የኦዲት ግኝት ክፍተት ባሳዩ ተቋማት ላይ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ምክር ቤቱ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አመላክተዋል።