09/07/2025
ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ
July 9, 2025 by ሥዩም ጌቱ
ኦነግ ባለፉት 50 ዓመታት ባከናወናቸው የፖለቲካ ትግሎች በርካታ ድሎች መገኘታቸውን ገልጾ ዛሬም ድረስ ግን ህዝቡ ሙሉ ነጻነት እንዳልተጎናጸፈ እንደሚያምን አስታውቋል። በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ምክንያት ዛሬም መታሰርና መሳደድ እንዳለ የገለጸው ኦንግ፤ ባለፉት7 ዓመታትም ችግሮችን በንግግር ወደመፍታት መሻገር አለመቻሉን ገምግሜያለሁ ብሏል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ)ለሁለት ቀናት ጉሌሌ በሚገኘው ዋና ቢሮው በማካሄድ ትናንት ባጠናቀቀው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው የፓርቲውን አሁናዊ ሁኔታን ጨምሮ የኦሮሚያ ክልል እና ኢትዮጵያ ብሎም የቀጣናው ተጨባጭ ይዞታዎችን መገምገሙን አስታውቋል፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በዚህ ላይ በሰጡን ተጨማሪ አስተያየት፤ “ፓርቲው ባለፉት አምስት ዓመታት ያለቢሮ መንቀሳቀስን ጫምሮ በርካታ ተግዳሮቶችን አሳልፏል” በማለት በዚህን ወቅት በየጊዜው መገናኘት የነበረበት የፖለቲካ ድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሳይገናኝ የቆየበትና የአመራሮች ከፓርቲው መውጣትን ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች የገጠሙበት በመሆኑ ችግሩን እልባት በመስጠት የወደፊቱን አቅጣጫ ማስቀመጥ የአሁኑ የማዕከላዊ ኮሚተው ዋና ዋናዎቹ ትኩረት ናቸውም ብለዋል፡፡
ፓርቲው በውይይቱ ወቅታዊውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በተመለከተ ፓርቲው ባሳለፈው አምስት ዓመታት የገጠሙትን ተግዳሮች ገምግሞ የወደፊት አቅጣጫውን አስቀምጧል ተብሏልም፡፡ ከመስከረም 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አገር ቤት በመመለስ አዲስ አበባ የነበረውን ቢሮውን ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የከፈተው ኦነግ አገሪቱ ያስቀመጠቻቸው ህጋዊ መሰረቶችን በማሟላት በሰላማዊ መንገድም ለመንቀሳቀስ ፈቃድ ማግኘቱን በመጥቀስ፤ አሁን ላይ የተፈጠሩትን ክፍተቶች ለመድፈን በአጭር ጊዜ ውስጥ 5ኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ ለማድረግ ኮሚቴ ማዋቀሩንም አስታውቋል፡፡
ፓርቲው “ያለአግባብ ከፓርቲው የወጡ” ያሏቸውን የፓርቲው አመራር አባላትን በማስመልከት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አመራር አባላቱን ከፓርቲው ያገለለ መሆኑንና ይህንኑን ውሳኔ ለፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ለማቅረብ አቅጣጫ ስለመቀመጡን ነው የተጠቆመው፡፡ ቃል አቀባዩ አቶ ለሚ በነዚህም ጉዳዮች ላይ በሰጡን ተጨማሪ ማብራሪያ፤ “ውሳኔዎቹም አንደኛው የፓርቲው አምስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የጠራበት ሲሆን ከድርጅቱ በራሳቸው ጊዜ የወጡ አመራር አባላቶችን በማገድ ውሳኔውን ነለጠቅላላ ጉባኤው ለማሳለፍ ተወስኗልም” ነው ያሉት፡፡
በክልላዊ፣ አገራዊ እና አህጉራዊ ብሎም ቀጣናዊ አሁናዊ ሁኔታዎች ላይ የሚስተዋሉ እውነታዎችን የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በስብሰባው መገምገሙንም ያወሱት አቶ ለሚ ፓርቲያቸው በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እውን ሊሆኑ የሚችሉበት መንገድ ላይም ምክረሃሳብ ማስቀመጡን አንስተዋል፡፡ እንደፓርቲቸው “ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ህዝባዊ ጽናትና ድርጅታዊ አንድነት አስፈላጊ ነው” በማለት አስተያየት ሰየሰጡት ፖለቲከኛው “ውስብስብ” ካሉት ከወቅታዊው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁናቴ መውጣትም የሚቻለው ዴሞክራሲን በማስፈን እንደሆነም ነው በአስተያየታቸው ያብራሩት፡፡
ፓርቲው በውይይቱ ወቅታዊውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በተመለከተ ፓርቲው ባሳለፈው አምስት ዓመታት የገጠሙትን ተግዳሮች ገምግሞ የወደፊት አቅጣጫውን አስቀምጧል ተብሏልም፡፡
ምስል፦ Seyoum
ኦነግ በሰሞነኛው ማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ ድርጅቱ ባለፉት 50 ዓመታት ባከናወናቸው የፖለቲካ ትግል በርካታ ድሎች መገኘታቸውን እንደሚያምን ገልጾ፤ ይሁንና ዛሬም ድረስ ህዝቡ ሙሉ የሆነን ነጻነት እንዳልተጎናጸፈ እንደሚምን በመግለጫው አብራርቷል፡፡ በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ምክንያት ዛሬም መታሰርና መሳደድ እንዳለም የገለጸው ኦንግ፤ ባለፉት ሰባት ዓመታትም ችግሮችን በንግግር ወደመፍታት መሻገር አለመቻሉን ገምግሜያለሁ ብሏል፡፡
ኦነግ “በአስመራ ከተገባው ስምምነት በተቃራኒ ባለፉት ሰባት ዓመታት የፓርቲውን አመራሮች እና አባላትን በማሳደድ የፖለቲካ ደባ ተፈጽሞብኛል” ያለ ሲሆን በኦሮሚያ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በርካቶች በፓርቲው ስም የምንቀሳቀሱ ያለአግባብ እስር ማቀው ታይተዋል በሚል ገምግሟልም፡፡
ኦነግ የተለመደ ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድ ላይ ትችት በማቅረብም መንግስት የህዝብን ደህነነት አደጋ ላይ የሚጥል ያለውን የሰላማዊ ፖለቲካ ምህዳር መጥበብን እልባት እንዲሰጥ ሲል ጥሪ አቅርቧልም፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ