09/07/2025
የነብያት ውርስ በ«ዘመናዊነት» ሚዛን ስም አይዋረድም!
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የጋራ ፎረም
የነብያት ውርስ በ«ዘመናዊነት» ሚዛን ስም አይዋረድም!
ሐምሌ 02 ቀን 2017 ፡ አዲስአበባ፣ ኢትዮጵያ
"ዑለማ" የሚለው ቃል በእስልምና ውስጥ ከፍተኛውን የእውቀት ደረጃ የተቆናጠጡ የማህበረሰቡ መንፈሳዊ መምህራንና የአዕምሮ መሪዎች የሆኑትን የነብያት ወራሾች የሚገልፅ የክብር ስያሜ ነው። አንድ ዓሊም ይህንን የክብር ደረጃ ለማግኘት እንደ ቁርኣን ትርጓሜ (ተፍሲር)፣ የሐዲስ እውቀት (ኩቱበ-ሲታን ጨምሮ)፣ እስላማዊ የህግ ስርዓት (ፊቅህ)፣ የህግ መነሻ መርሆች (ኡሱለል-ፊቅህ)፣ ስነ-መለኮት (አቂዳ) እና የዓረብኛ ቋንቋ ሰዋሰው (ነህው እና ሶርፍ) ያሉትን የእውቀት ዘርፎች ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል። ይህ ሁሉ እውቀት ሲደመር፣ ለመሪነት የሚያበቃ ልዩ "ግርማ" ይሰጣቸዋል፤ ይህም በስልጣን የሚገኝ ጉልበት ሳይሆን ከመንፈሳዊ ብስለት የሚመነጭ ፣በሰዎች ልብ ውስጥ መተማመንንና መረጋጋትን የሚዘራ የተፈጥሮ ስበት ነው።
ከዚህም ባሻገር እነዚህ የእውቀት ዘርፎች ከዘመናዊው አለም የተፋቱ አይደሉም፤ አንድ የፊቅህ ሊቅ የህብረተሰቡን ማህበራዊ አወቃቀር (ሶሺዮሎጂ)፣ የፍትህ መርሆችን (ህግ) እና የንግድ ስርዓቶችን (ኢኮኖሚክስ) ሳይረዳ የህግ ፍርድ ሊሰጥ አይችልም። ለዚህ ደግሞ ታሪክ ራሱ ህያው ምስክር ነው፤ አለም በዘመናዊ ሳይንስ ከመራቀቋ በፊት የበራችው እንደ አል-ሑሰይን ኢብን ዐብደላህ ኢብን ሲና ባሉ በህክምናና በፍልስፍና በተራቀቁና እስካሁን በዘርፉ ማጣቀሻ (Reference) መሆን በቻሉ የኢስላም ልጆች ጥበብ ነበር፤ በሒሳብ ዘርፍ ብንመለከት አል ጀብራ እንደ ሙሐመድ ኢብን ሙሳ አል-ኸዋሪዝሚ ባሉ ሊቃውንት ተፈጥሮ ለአለም ሲበረከት ፣የስነ-ፈለክ (አስትሮኖሚ) እና የጂኦግራፊ ሳይንስ ደግሞ እንደ አቡ ረይሓን አል ቢሩኒ ባሉ ምሁራን የኢስላም ልጆች ሲመራ ነበር።
ይህ የጥበብ አመራር የሩቅ ዘመን ቅርስ ብቻም አይደለም፤ የራሳችን የኢትዮጵያ መጅሊስ እጅግ ፈታኝ በነበረ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ሲመሰረት፣ ተቋሙ በፅናት እንዲቆምና ህዝበ ሙስሊሙን በአንድነት እንዲመራ ያደረገው፣ እንደ ክቡር ሸይኽ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ያሉ አባቶች የነበራቸው የብስለት አመራርና የጥበብ ልህቀት ነው። ስለሆነም የዛሬዎቹን ዑለሞች ከዚህ የበለፀገ ታሪካዊና አዕምሯዊ ውርሳቸው ነጥሎ መመልከት ለራሱ ለእውቀት ታሪክ ጀርባን እንደመስጠት ይቆጠራል።
በማህበረሰባችን ውስጥ የሚነሱ ውይይቶች ወደ እድገት የሚያመሩ መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ሲሆን፣ የውይይቱ ሚዛን ሲዛባና የመለኪያ መስፈርቱ ሲሰፋ ግን አቅጣጫውን ስቶ ወደ ማፍረስ ያመራል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የነብያት ወራሾች በሆኑት በክቡራን ዑለሞቻችን ላይ እያተኮረ ያለው ዘመቻ ፣የዚህ የተዛባ ሚዛን ህያው ማሳያ ሆኗል። ይህ ጉዳይ የጥበብን ውቅያኖስ በወረቀት ሰርተፊኬት ለመለካት የሚደረግ አደገኛ ሙከራ ነው፤ የመንፈስን ልዕልና በአስተዳደራዊ ችሎታ ለመመዘን የሚደረግ መሰረታዊ ስህተት ነው። ይህ ዘመቻ የአስተሳሰብ ልዕልናን ሳይሆን የአመለካከት ድህነትን ይዞ የቀረበ፣ የነብያትን ውርስ የተሸከሙትን ትከሻዎች በቀላል አስተዳደራዊ መመዘኛዎች ክብደት ዝቅ ለማድረግ የሚሞክር፣ ለራሱ ለውርሱ ክብር የማይሰጥ "የተሃድሶ" ቃና ያዘለ አካሄድ ነው።
የኢትዮጵያዊ ዓሊም የእውቀት ፍለጋ ጉዞ በምቾትና በቅንጦት የተሞላ ሳይሆን በራሱ አንድ ትልቅ የህይወት ተጋድሎ ነው። ከቤተሰብ ተለይቶ ለዓመታት የሚዘልቅ የስደትና የልፋት ህይወት ሲመርጥ፣ የሚመራው የእውነት ጥማት እንጂ የሹመትና የዝና ጥማት አይደለም። በየገጠሩ ከመስጂድ መስጂድ እየተንከራተተ ፣ በዑለሞች ጉልበት ስር ተንበርክኮ፣ ሌሊቱን በብርድ፣ ቀኑን ሀሩር እና በርሃብ አለንጋ ተገርፎ እያሳለፈ የሚገነባው የእውቀት ግንብ በቀላል ንፋስ የሚናድ አይደለም። ይህ በላብና በእንባ የተገነባ የህይወት ልምድ፣ ከገፆች የሚነበብ እውቀት ብቻ ሳይሆን የህይወትን ትርጉም፣ የሰውን ልጅ ስቃይና የማህበረሰብን የልብ ትርታ የሚያስተምር ጥልቅ የህይወት ዩኒቨርሲቲ ነው።
ይህንን እድሜ ልክ የፈጀ የመንፈስና የአዕምሮ ተጋድሎ በዘመናዊው ቢሮክራሲ በተቀመጡ የአማርኛ ፊደል አጣጣልና የ8ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ወረቀት ጋር ማነፃፀሩ የችግሩን ምንጭ መሳት ነው። አንድ ዕድሜውን ሙሉ ውስብስብ የፊቅህ ትንታኔዎችንና የቁርኣን ምስጢሮችን ሲያጠና የኖረ ዓሊም፣ በዘመናዊው አስተዳደር የተቀመጠው መስፈርት ቢያንሰው ፣ይህ የዓሊሙን ድክመት ሳይሆን የስርዓቱን ክፍተትና የእይታ ማነስ ነው የሚያሳየው። ኢስላማዊውን የእውቀት ስርዓት በማኮሰስና ክፍተቶችን በማጉላት፣ መፍትሄውን በአንድ የአሰራር ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ጠቅልሎ ለማቅረብ መሞከር፣ ለችግሩ ከልብ ከማሰብ ይልቅ ለቀረበው የመፍትሄ ሀሳብ ድርጅታዊ ገበያ የመፍጠር ዘመቻ ያስመስለዋል። ችግሩ የዓሊሙ አለማወቅ ሳይሆን ጥበቡን ለመጠቀም የሚያስችል ድልድይና አጋዥ መዋቅር አለመዘርጋቱ ነው። መፍትሄውም ጥበበኛውን ከደጅ ማስቀረት ሳይሆን የፅሑፍና የአስተዳደር ስራዎችን የሚያግዙለት ባለሙያዎችን በማቅረብ ጥበቡ ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ ነው።
ይህንን ተከትሎ የሚመጣው ሌላኛው አደገኛ አካሄድ ዑለሞች በማህበረሰቡ መሪነት ላይ ያላቸውን ድርሻና ፍላጎት እንደ ስልጣን ጥማትና ወንበር ፍቅር አድርጎ መተርጎም ነው። ይህ እጅግ አደገኛና ስር የሰደደ አንድምታ ያለው ስህተት ነው። የዓሊም መሪነት ፍላጎት የሚመነጨው ከስልጣን ፍቅር ሳይሆን ከተጠያቂነት ስሜት ነው።
በብዙ ተጋድሎና ትግል ለተመሰረተው የኡለማ ምክር ቤትን የህዝብ ቁቡልነትን ለማሳጣት በጊዜያዊ ልዩነት «ለይስሙላ የተቋቋመ» በሚል ማኮሰስ ክፍተቱን አይሞላም።
ዑለማዎቻችን የነብያት ወራሽ እንደመሆናቸው ማህበረሰቡን በመንፈሳዊና በሞራል ጉዳዮች የመምራት አደራ እንዳለባቸው ያምናሉ። ይህንን አደራ ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ "ስልጣን ፈላጊ" የሚል ታርጋ መለጠፍ ሚናቸውን ወደ ተራ ፖለቲካዊ ሽኩቻ ማውረድ ነው። ይህ አካሄድ እያንዳንዱን ፈትዋ በፖለቲካዊ ሚዛን እንዲለካ እያንዳንዱን ምክር በስልጣን ሽኩቻ መነፅር እንዲታይ በማድረግ የዲኑን ንፅህና ያደፈርሳል። በመጨረሻም ማህበረሰቡን ከመንፈሳዊ መሪዎቹ በመነጠል፣ ልጓም እንደሌለው ፈረስ ለፈተና ያጋልጠዋል።
በዚህ ዘመቻ ውስጥ እንደ አማራጭ የቀረበው "ዘመናዊ" የተባለው የአደረጃጀት መዋቅር ግቡ በቁጥር የሚለካ ውጤት የሆነውን የኮርፖሬት ፍልስፍና ወደ ኢስላማዊ ተቋም ለማስገባት ይሞክራል። ይህን መሰል ተቋም ዋና ግብ ግን የኡማውን መንፈሳዊ አንድነትና የዲኑን ክብር ማስጠበቅ እንጂ በሪፖርት የሚለካ ቅልጥፍና አይደለም።
መፍትሄው መዋቅር አልባ መሆን ሳይሆን የራሳችንን የበለፀገ የአመራር ጥበብ መጠቀም ነው። ኢስላም በሹራ (ምክክር)፣ በአማና (ታማኝነት)፣ በዐድል (ፍትህ) ና በሒክማ (ጥበብ) ላይ የተመሰረተ የአመራር መርህ አለው። ስለዚህ ዋናው ተግባር፣ አሰራራችንን እስላማዊ ማድረግ እንጂ እስልምናችንን ኮርፖሬቲካዊ ማድረግ የለብንም። ይህ ማለት ግን ዘመናዊ የአሰራር መሳሪያዎችንና ግልፀኝነትን የሚያሰፍኑ ስልቶችን እንቃወማለን ማለት አይደለም። ይልቁንም እነዚህ መሳሪያዎች በሙሉ የኢስላማዊ መርሆቻችን ተገዥና አገልጋይ ሆነው መንፈሳዊ ግባችንን እንዲያሳኩ ማድረግ አለብን ማለት ነው።
የሚገርመውም ይህ የትችትና የመመዘኛ ሚዛን በአንድ በኩል ብቻ ያጋደለ መሆኑ ነው። ዑለሞች ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ የሚጮኸው ድምፅ፣ የዘመናዊ ትምህርት ምሁራን ደግሞ በዑለማ ጉልበት ስር ተንበርክከው የዲኑን ጥልቅ እውቀት እንዲማሩ የሚጠይቅ ተመሳሳይ ጉልበት ያለው ድምፅ አያሰማም። ይህ የተዛባ አመክንዮ፣ አላማው መተጋገዝና መሞላላት ሳይሆን የዑለሞችን ተፈጥሯዊ የመሪነት ሚና ለመንጠቅ የሚደረግ ስውር ዘመቻ አካል ነው።
ይህ ማለት የህግ ባለሙያው፣ የፋይናንስ ምሁሩ፣ የሚዲያና ቴክኖሎጂ የመሳሰሉት ባለሙያዎች ሚና የላቸውም ማለት አይደለም። ልዩነቱ ያለው ስለ ሚና መኖርና አለመኖር ሳይሆን ስለ ስፍራና ቅደም ተከተል ነው። ልብና አዕምሮ በሌለበት እጅና እግር ብቻቸውን ትርጉም እንደሌላቸው ሁሉ የመሪነት ጥበብና መንፈሳዊ አቅጣጫ ከሌለ የባለሙያዎች ክህሎት ብቻውን ማህበረሰቡን ወደ ትክክለኛው መዳረሻ ሊያደርሰው አይችልም። አመራሩ የጥበብና የብስለት ሲሆን ክህሎት ደግሞ የዚያ አመራር አስፈፃሚና አጋዥ ክንፍ ይሆናል።
ስለሆነም እኛ የምንመኘው ትግል አንዱ ሌላውን የሚያሳንስበት ሳይሆን ሁሉም በቦታው የሚከበርበትን ስርዓት መገንባት ነው። የምንመኘው ተቋም የፊቅህ ሊቃውንት የሆኑት ዑለሞች ስለ አንድ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ውል ኢስላማዊ ፍርድ ከሰጡ በኋላ፣ በዘመናዊ የህግና ኢኮኖሚ ትምህርት የቀሰሙ ባለሙያዎች ደግሞ ያንን ፍርድ መሰረት አድርገው ህጋዊ ሰነዶችን የሚያዘጋጁበትን ነው፤ ዑለሞች የመንፈሳዊ ዳዕዋ አቅጣጫን ሲወስኑ፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ደግሞ ያንን መልዕክት በዘመኑ ቋንቋና ቴክኖሎጂ ለህዝብ የሚያደርሱበትን ስርዓት ነው። እውነተኛ ዘመናዊነት ማለት ይህ ነው፤ ጥበብን በክህሎት ማገዝና ማገልገል።
ከፊታችን ያለው አማራጭ የአሰራር ዘዴን ስለማሻሻል ሳይሆን የተቋማችንን ነፍስና የህዝባችንን አደራ ስለመጠበቅ ነው። እውነተኛ ዘመናዊነት ማለት ያለፈውን ጥበብ አውርሶ ለዛሬው ችግር መፍትሄ የሚሰጥ ለነገው ተስፋ የሚሆን ማንነትን መገንባት እንጂ፣ የሌሎችን ልብስ ለብሶ እንደመራመድ አይደለም። ስለዚህ ትክክለኛው መንገድ የማህበረሰቡ ልብና አዕምሮ የሆኑትን ዑለሞች በአመራር ማዕከል ላይ እንደ ፀሀይ ማስቀመጥና የዘመኑን ክህሎት የያዙትን እንደ ብርቱ ክንፎች አድርጎ ለስኬት መብረር ነው። ከዚህ ውጪ ያለው መንገድ ስርን ቆርጦ ቅርጫፍ ላይ የሚደረግ ውይይት ከመሆኑም በላይ የነብያት ወራሾችን ከዙፋናቸው አውርዶ በተራ አስተዳዳሪዎች ለመተካት መሞከር ነው። ይህም ለማህበረሰቡ መንፈሳዊ ህልውና ፍፁም አጥፊ ነው።
በዘመናዊነት ስም የዑለማን ክብር የማኮሰስ ዘመቻ ሊቆም ይገባል!
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የጋራ ፎረም
ሐምሌ 02 ቀን 2017 አዲስ አበባ ፣ ኢትዮጵያ