04/06/2026
#ወንድሜ!
ወልደህ ባታውቅ ነው እንጂ ልጅን ወልዶ ማሳደግ፣ ለቁምነገር ማብቃት እጅግ ከባድ ነዉ። በየእድሜዉ እርከን ብዙ ጭንቀት አለዉ:- ፅንሱ ይፀና ይሆን? በሰላም ይወለድ ይሆን? ጤናማ ሆኖ ይወለድ ይሆን? ጡት ይጠባ ይሆን? በሆነ በሽታ ይቀሰፍ ይሆን? ከእጅ ወድቆ ይቀጭ ይሆን? ሲጫወት አደጋ ይደርስበት ይሆን? በሌላ ሰዉ እጅ ይበደል ይሆን? ለእድገቱ በቂ ነገር ያገኝ ይሆን? ተምሮ ይወጣ ይሆን? በሰላም ወጥቶ ይመለስ ይሆን? ፈጣሪዉን አዉቆ ይፈራ ይሆን? ወዘተ.። አንተም ተወልደህ ያደግከዉ ወላጆችህ በዚህ አይነት ጭንቀት ዉስጥ አልፈዉ ነዉ።
ግን በስተመጨረሻ እነሱ ያላሰቡት አንድ ጭንቀት እዉን ሆነ:- በጭንቅ ወልደዉ በመከራ ያሳደጉት ልጃቸዉ በዋዛ ሌሎች ወላጆች በጭንቅ ወልደዉ በመከራ ያሳደጓቸውን ልጆች ያለምንም ርኅራኄ በጥይት የሚቆላቸዉ ሆኖ አረፈ። ከልጆችም አልፎ ወላጆችንም ጭምር የማይምር ጭራቅ ወጣዉ። ለወላጆችህ በዚህ መልክ ህመም፣ ለወገንህ ቁስል፣ ለሀገርህ ደግሞ ኪሳራ ለመሆን በቃህ። ከፈጠረህ አምላክ ይልቅ የተረገመዉ ዲያብሎስ ከበረ። ይኸዉ ነዉ ያንተ ታሪክ፣ እራስህ ምዕራፉን ካልዘጋህ ቃልህ ሆኖ ለዘለዓለም ይቀመጣል።
ሰላም ይሁን! 🥺🥺