24/07/2025
ዘር መቁጠር የተፈጠርክበት አላማ አይደለም!
#ትኩረት:-ይህንን ፅሁፍ በገለልተኝት ስሜትና እራስህን እንደ አንድ ከእናትና አባትህ የተገኘህ የፈጣሪ ግኝት እንጂ ሌላ ተዓምር እንዳልሆንክ እያሰብክ አንብበው።
"የእኔ ዘሮች የፈጣሪ ድንቅ ፍጡራን የሆኑት የሰው ልጆች በጠቅላላ ናቸው"
✍️አብዛኛው ጊዜ ህይወታችን ትርጉም የሚያጣው ልንቆጣጠራቸው ከማንችላቸው ነገሮች ይልቅ ልንቆጣጠራቸው ወይም ከመቆጣጠርም አልፈን ልናጠፋቸው በምንችላቸው ነገሮች ነው።
አሁን ያለንበት ተጨባጭም ይኸው ነው።በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አይደል የሚባለው? ዘረኝነት የሚባለው ትልቁን ነቀርሳ የብዙዎቻችን አዕምሮ አውሮታል።በእርግጥ እውነት ነው ሁላችንም ከአንድ እናትና አባት አልተገኘንም።
ሁሉንም በተለያየ የሀገራችን ክልል ውስጥ ከተለያዩ ጎሳዎችና ከተለያዩ እናትና አባቶች ተገኝተናል።
ነገር ግን ለምንም ነገር ምክንያታዊ መሆን አስፈላጊ ነው።በተለይም የተማርክና ራስህን በራስህ የመምራት አቅም ያለህ ሰው ከሆንክ።
አለመማርህና የአስተሳሰብ ግድፈት(ደካማነት ) እንዳለብህ የምታውቀው አሁን ያለህ ምንነት(አፋርነትህ,ሶማሌነትህ,ጋምቤላነትህ) ወይም ሌሎችም ውስጥ መፈጠርህ ያንተ ምርጫ እና ባንተ ፈቃድ የተከወነ ነገር አድርገህ ማሰብ ስትጀምር ነው።
ሁሌም ራስህን መጠየቅ ያለብህ አንድ ወሳኝ ጥያቄ ልንገርህ
#ፈጣሪ አንተን ሌላ ቦታ(ክልል) ላይ መፍጠር እየቻለ አሁን በተፈጠርክበት ቦታ(ክልል) እንድትፈጠር ማድረጉ ለምን ይመስልሀል?
ፈጣሪ በተለያዩ ዘሮች ከፋፍሎ የፈጠረን እንድንተዋወቅና እንድንዋደድ በሚል ቢቻ እንጂ ዘርን እየቆጠርን ዘሮችን እንድናጠፋ አልነበረም።ወይም ትክክለኛ የዘር አቆጣጠሩን ተጠቅመህ ዘርህን ከ አደም ጀምረህ ቁጠር የዛኔ ሁሉም ያንተ ዘር እንደሆነ ይገባሀል።
ሁላችንም በራሳችን ምርጫ ያልተፈጠርንና ከአደም የተገኘን መሰረታችን አንድ የሆንን ሰዎች እንጂ ሌላ አይደለንም።
አየህ! አንድም ቀን ይህንን በዚህ ልክ አስበነው አናውቅም።የተፈጠርንበት አላማና እየኖርነው ያለው ህይወት ለየቅል ሆኖ ተምታታብን።ዘረኝነትን በሚገባ ማጥፋትና ፍቅራችንን ማጠናከር የምንችለው ዘር መቁጠራችን ምን ያክል ኋላቀርነትና ነፍስን መበደል እንደሆነ መረዳት ስንችል ነው።
አስተውሉ! ይህ የምትኖረው ህይወት ያንተ እንጂ የማንም አይደለም።ይህንን ፅሁፍ ካነበብክ በኋላ ለራስህ ''የእኔ ዘሮች የፈጣሪ ተዓምራዊ እና ድንቅ ፍጡር የሆኑት የሰው ልጆች በሙሉ ናቸው!'' ብለህ ንገረው።
ከዚያም ፅኑ አና ውስጣዊ ጥንካሬ ያለው አስተሳሰብ ይዘህ የግል ጥቅማቸውን በሚያራምዱ ሰዎች ጉትጎታ መታለልን አቁመህ ለህሊናህ ሰላም መኖር ጀምር።
ይህን መልዕክት አንተ ጋር ከደረሰ እጅህ ላይ እንዳታቆየው!
ሰላማችሁ ያብዛልኝ!