
21/03/2025
የእናት ባንክ " እማዬ " ቅርንጫፍ ስራ ጀመረ ።
👉 ይህን ምክንያት በማድረግ ለ10 ቀናት የሚቆይ ውድድር ይፋ አድርጓል ።
***************************************************
" እናት ባንክ " ከ11 ዓመት በፊት የገንዘብ አቅምን ከማሳደግና የግል ሀብትን ከመጨመር ያለፈ ራዕይ ባላቸው 11 እንስት ባለሀብቶች የተቋቋመ ባንክ መሆኑ ይታወቃል ። ባለ ራዕዮቹ ከዓላማቸው ስያሜያቸውን አወጡ ፤ " እናት ባንክ " ሲሉ ። ልክ እንደ እናት ያሉ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል ። እንደ መደበኛ ባንክ ለሁሉም ዜጋ እኩል ፣ በተለይ ደግሞ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የአቅም ውስንነት ሊቀርፉ የሚችሉ አማራጮችን በመተግበር ሴቶች ኢኮኖሚው ጉልህ ተሳትፎና ድርሻ እንዲኖራቸው ሲያደርጉ ቆይተዋል ።
እናት ባንክ የድካማቸውን ያህል ያልተነገረላቸውን ብዙሃን ኢትዮጵያውያን እናቶችን የሚወክል "እማዬ" የተሰኘ ቅርንጫፍ በይፋ ከፈተ። በመላ ሃገሪቱ ይሄንን "እማዬ" ቅርንጫፍን ሳይጨምር 206 ቅርንጫፎች ያሉት እናት ባንክ ከአሁን ቀደም በአዲስ አበባ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን ለሃገርና ለወገን የጎላ አስተዋጽዖ ያደረጉ ኢትዮጵያውያንና ጥቂትም ኢትዮጵያን ወዳድ የውጭ ሀገር እንስቶች ስም ሲሰይም ቆይቷል። አሁን ደግሞ በአይነቱ እጅግ የተለየና በአገልግሎቱም ከባንክ አገልግሎቶች የተሻገሩ ተግባራት የሚከወንበት ቅርንጫፉን " እማዬ ቅርንጫፍ " በሚል ስያሜ ትናንት በይፋ ከፍቷል። ይህ ቅርንጫፍ ለልጆቻቸው ሕይወታቸውን የሰጡ ፣ በጎ አርአያ የሆኑ ፣ እድሜያቸውን ሁሉ ፣ ሕይወታቸውን ሁሉ ለልጆቻቸው ሰጥተው ታሪክ ላልመዘገባቸው ፣ ስም ላልተሰጣቸው ፣ በመልክና በግብር ተለይተው " እገሊት " ተብለው ስም ላልወጣላቸው ለሁላችንም እናቶች ማስታወሻ እንዲሆን ነው " እማዬ ቅርንጫፍ " የተከፈተውና ትናንት ስራ የጀመረው ።
የቅርንጫፍ ባንኩን ስራ መጀመር ምክንያት በማድረግ ትናንት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው በተለይ " እማዬ ቅርንጫፍ " ን ምክንያት በማድረግ ካሁን ቀደም ባንኩ ለመላው ደንበኞቹ አውጥቶት መላው ደንበኞቹን ሲያወዳድርበት የነበረው " ለእናቴ " የጽሑፍ እና " የዓመቱ ድንቅ እናት " የጽሑፍ ወይም የድምጽ ወይም የምስል ውድድር ለ10ቀናት ብቻ ከዛሬ አርብ የካቲት 12/17 እስከ መጪው ቅዳሜ የካቲት 20/17 11:00 ሰዓት ድረስ የሚቆይ ውድድር አዘጋጅቷል ። ለውድድሩ የሚላኩት ጽሑፎች በአዲስ አበባ ፒያሳ አቡነ ጴጥሮስ መታሰቢያ ሐውልት አጠገብ የቀድሞው ኢትዮጵያ ሬዲዮ ወይም ብዙሀን መገናኛ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አዲሱ ( ከአወሊያ ት/ቤት ፊትለፊት ) ህንጻ ምድር ቤት በአካል እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ ተወዳዳሪዎች በአቅራቢያቸው የሚገኙ የእናት ባንክ ቅርንጫፎች በአካል ቀርበው ማስረከብ ይችላሉ ።
የውድድሩን መስፈርቶች ከታች ባለው ሊንክ ያገኙታል ።
https://www.facebook.com/share/14yYe9kf1h/