
12/02/2025
ዋርካ ሬዲዮ በአየር ዳግም ሊናኝ ነው፤ ከዕድሜያችን ቆርሰን ሰጥተን ጀምረነዋል፤ ዳርም ይደርሳል! እንኳን ደስ አለን!
ሕልሙ ሕልም ሆኖ ላይቀር - የስራ አመራሩ አዲስ ኃይልን ጨምሮ በብርቱ መንፈስ ከች ብሏል፡፡ ምስጋና እነሆ ለባለውለታዎች!!!
===========================
በመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ በብቃቱ ልቆ ተመራጭ ሚዲያ መሆንን ራዕዩ ያደረገው ኢትዮ ዋርካ አንዱ ፕሮጀክቱ “የሕብራዊነት ድምፅ” ሆኖ መዝለቅ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ፕሬስ_በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና በሸገር ሬዲዮ ውስጥ ጉልህ የስራ አመራር የነበረው አቶ ስለሺ ተሰማ (አንጋፋ ጋዜጠኛ) የዋርካ አዲሱ ዋና ስራ አስኪያጅ ነው የሆነው፡፡
ዋርካ FM ሬዲዮ 104.1 ለአየር በቅቶ ወደተወዳጆቹ ኢትዮጵያውያን ከወደ ሙከራ ስርጭት መመለስ ባሻገር በቅርቡ መደበኛ ፕሮግራሞችን ለመጀመርም እየተንደረደረ ይገኛል፡፡
ኢትዮ ዋርካ የጠቅላላ ጉባኤውን መደበኛና ድንገተኛ ስብሰባዎቹን በጊዮን ሆቴል አካሂዶ ዋነና ውሳኔዎቹን በቃለ ጉባኤ ማፀደቁን ተከትሎ የተለያዩ ለመጪ ጉዞው ወሳኝ የሆኑ አዳዲስ አመራሮችን አካቶ በአዲስ የተነቃቃ መንፈስ ወደስራ ገብቷል፡፡
አዲሱ አመራር ስቱዲዮ ከማመቻቸት አንስቶ የታዳሚን ቀልብ ይዞ ለመዝለቅ የሚያስችለውን አዲስ የስትራቴጂ አቅጣጫ እየነደፈ በፍጥነት ወደአየር ተመልሶ ለመምጣት እየተንደረደረ ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ የዋርካን ፅንስ ከመጠንሰስ አንስቶ ረዥሙን ውጣ ውረድ በፅናት ይዘው የተሻገሩ ኃላፊነት የሚሰማቸውን ግንባር ቀደሞቹን አይታክቴ ጥቂት የስራ አመራር ሰጪዎችን እንዲሁም ተስፋ አድርገው ገንዘባቸውን ወደአክሲዮኑ ሂሳብ በጉጉት ያስገቡትን አባላት እና በሀሳብ ሁሌም ውሳኔ ሰጪውን አካል በስልክም በአካልም ተገኝተው ድጋፍ ያደረጉትንም እንዲሁ ሳናመሰግን አናልፍም፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣንን እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ክብረት ይስጥልን አያልን፤ ከስራ አመራር ቦርድ ደግም ተስፋ ባለመቁረጥ ቅንነትና ፅናታቸው ጎልቶ የማይዘነጋ ቢሆንም የስራ ግዴታቸው አድርገው ቀን ከቀን የኩባንያውን ህልም ለማዝለቅ የሚታትሩት ልባቸው ያውቀዋልና በስም ሳንጠቅስ ምስጋናቸውን ይውሰዱ!
ዋርካ በመጪው አስርት አመታት በምስራቅ አፍሪካ የተለየ ምርጥ ሚዲያ ሆኖ ልቆ እንደሚወጣ ይታመናል፡፡
ኩባንያው ከብዙሀን መገናኛው የሬዲዮ ስራ በትይዩ በጥናትና የማማከር አገልግሎት ተሰማርቶ የቢዝነስ ሞዴል ቅኝቱን እንዲያጠናክር ጉባኤው አሳሰቦ በጫረታ አሸንፎ የያዘውን ሞገድ ኤፍ ኤም 104.1 ሬዲዮን በፍጥነት ለአየር እንዲያበቃ አደራ ብለዋል፡፡
ስራዎችንም በአዲስ መንፈስ በፍጥነት ለማከናወን እንዲያስችለው አዲስ ካፒታል ለመሳብ እንዲያስችለው አዳዲስ አባላትን ለመቀበል እና ለቦርዱም ተጨማሪ ስልጣን መስጠት ከተላለፉት ውሳኔዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ዘጠኝ አባላት ያሉት የስራ አመራር ቦርድ ተመርጦና አዲስ ዋና ስራ አስኪያጅ ተሰይሞ ስራው የቀጠለ ሲሆን የአክሲዮን አባላቱም ሆነ በተለይም የስራ አመራር ቦርዱ ኩባንያውን አላራምድ ብሎት የቆየው የፋይናንስ ውሱንነት እንደነበር በቁጭት አውስተዋል፡፡