FMC Sport

FMC Sport Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from FMC Sport, Media/News Company, Addis Ababa.

የሊዮኔል ሜሲ የመጨረሻ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታአዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ኮከቡ አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ እስካሁን ድረስ ለሀገሩ 207 ሰባት ጨዋታዎችን አድ...
06/10/2026

የሊዮኔል ሜሲ የመጨረሻ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ኮከቡ አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ እስካሁን ድረስ ለሀገሩ 207 ሰባት ጨዋታዎችን አድርጓል።

በዚህ አስተዋጽኦው የብሔራዊ ቡድኑ የምንም ጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክብረ ወሰንን ይዟል።

በአርጀንቲና ርዕሰ መዲና ቦነስ አይረስ በሚገኘው ሞኑመንታል ስታዲየም ከቤኒን ጋር በሚደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ለሀገሩ 208ኛ ጊዜ በመሰለፍ የስንብት ጨዋታውን ያደርጋል።

ሜሲ በአርጀንቲና ታሪክ ከምንጊዜም ታላላቅ ተጫዋቾች ቀዳሚው ነው። በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ከስፔን ጋር ለፍጻሜ የተጫወተችው አርጀንቲና ሽንፈትን ካስተናገደች ከሳምንታት በኋላ ‘ከእንግዲህ የምሰጠው ምንም ነገር የለኝም’ በማለት ከብሔራዊ ቡድን ራሱን እንደሚያገል አስታውቆ ነበር።

ሜሲ ይህንን ውሳኔውን ይፋ ቢያደርግም አሰልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ በብሔራዊ ቡድኑ ሜሲ የመቀጠል ፍላጎት ካለው በሩ ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል።

ከብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ በሚያደርገው ጨዋታ የሚሰናበተው ሜሲ የክለብ ስራውን በመቀጠል ከኢንተር ማያሚ ጋር ባለው በየዓመቱ የሚታደስ ውል መሰረት እስከ 2028 የውድድር ዘመን መጨረሻ ድረስ ይቆያል።

ሜሲ ወደፊት የሚጠብቀው ነገር አሁንም ግልጽ እየሆነ ነው። እግር ኳስን ሳይለቅ ይቀጥላል፣ ምክንያቱም ያለ እግር ኳስ መኖር ለእሱ አስቸጋሪ ይሆናል። ነገር ግን ሌሎች የንግድ ስራዎቹ ከእግር ኳስ ዓለም በጣም የራቁ ናቸው።

ኒውዌልስ ኦልድ ቦይስ ከሜሲ ጋር ቅርብ ሆኖ ይቆያል። ክለቡ በዚህ ዓመት በሚደረገው የሜሲ ካፕ ከሚሳተፉ 16 አካዳሚዎች አንዱ ነው።

ክለቦችን መያዝ አንዱ ፍቅሩ ከሆነ፣ የወጣቶች እግር ኳስ ሌላኛው ነው። በልጁ ጨዋታዎች ላይ በመደበኛነት መገኘቱና በሜሲ ካፕ ላይ የሚያሳየው ተሳትፎ ይህንን ያሳያል።

ሜሲ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ የአካዳሚ ቡድኖች የሚዘጋጀውን ውድድር በገንዘቡም በጊዜውም ይደግፋል።

ከሜዳ ውጭ ሜሲ ትልቅ የንግድ ስራ አውታር ገንብቷል። ይህም ፎርብስ በሰኔ ወር የሀብቱ መጠን ወደ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር እንደሚገመት እንዲገልጽ አድርጎታል። ባለፈው ዓመትም ከእግር ኳስና ከንግድ ስራ የተገኘ ገቢው ወደ 140 ሚሊየን ዶላር ነበር።

የሜሲ ታዋቂ የማስታወቂያ ስምምነት ከአዲዳስ ጋር የፈረመው የዕድሜ ልክ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ነው።

በንግድ ስራው ደግሞ ኤምአይኤም ሆቴልስ (MiM Hotels) ትልቁ ቢዝነሱ ነው።

በአቤል ነዋይ

ትዕግስት አሰፋ የዓመቱ ኮከብ አትሌቶች ሽልማት እጩ ሆነችአዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም አትሌቲክስ የ2026 የዓለም ምርጥ አትሌት ሽልማት እጩዎችን ዝርዝር ይፋ...
06/10/2026

ትዕግስት አሰፋ የዓመቱ ኮከብ አትሌቶች ሽልማት እጩ ሆነች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም አትሌቲክስ የ2026 የዓለም ምርጥ አትሌት ሽልማት እጩዎችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም አትሌት ትዕግስት አሰፋ በሴቶች ዘርፍ ከታጩት 10 አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትታለች።

አትሌት ትዕግስት በበርሊን ማራቶን 2:11:04 በሆነ ጊዜ ድል በማድረግ 3ኛ የበርሊን ድሏን ያስመዘገበች ሲሆን÷ ይህም በሴቶች ማራቶን ታሪክ 3ኛው ፈጣን ሰዓት ነው፡፡

በሚያዝያ ወር የለንደን ማራቶንን በ2:15:41 በማሸነፍ የሴቶች ብቻ የዓለም ክብረወሰን ማስመዝገቧም ይታወሳል፡፡

ድምጽ የመስጠቱ ሒደት ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።

የዓመቱ ምርጥ ወጣት አትሌቶች ፣ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ እና የፕሬዚዳንቱ ሽልማት ሕዳር 20 ቀን 2019 ዓ.ም በሞናኮ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሽልማት መርሐ ግብር ላይ የሚታወቅ ይሆናል፡፡

በ2ኛው የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ አትሌት ጂራታ ሌሊሳ እና ብርነሽ ደሴ አሸነፉአዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በቢሾፍቱ በተካሄደው 2ኛው የ10ኪ.ሜ የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ ውድድር ...
01/10/2026

በ2ኛው የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ አትሌት ጂራታ ሌሊሳ እና ብርነሽ ደሴ አሸነፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በቢሾፍቱ በተካሄደው 2ኛው የ10ኪ.ሜ የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ በወንዶች ጂራታ ሌሊሳ፣ በሴቶች ብርነሽ ደሴ አሸናፊ ሆኑ።

ውድድሩ “ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ቃል በቢሾፍቱ ከተማ በኦሮሚያ ባህልና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት ነው የተካሔደው።

10 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው በዚህ ውድድር ላይ የዩጋንዳ እና የታንዛንያ አትሌቶችን ጨምሮ ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል።

በውድድሩ ከፍተኛ ፉክክር በተደረገበት በወንዶች የሸገር ከተማው ተወዳዳሪ ጂራታ ሌሊሳ ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ከሸገር ከተማው ለሚ ተሾመ ሁለተኛ እና ዩጋንዳዊው አቤል ቺቤት ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በሴቶች በኩል የተደረገውን ብርቱ ፉክክር ብርነሽ ደሴ በበላይነት የጨረሰች ሲሆን፣ አዳኑ ዴኮ ከሸገር ከተማ ሁለተኛ እንዲሁም ዝማም ባራኪ ከንግድ ባንክ ሦስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል።

በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ ለሆኑት አትሌቶች 1ሚሊየን ብር እና ዋንጫ ተበርክቷል።

ሁለተኛ ሆነው ላጠናቀቁት ደግሞ 750 ሺህ ብር ፤ በሶስተኛ ደረጃ ይዘው ላጠናቀቁት ደግሞ 500 ሺህ ብር እንዲሁም ከ4ኛ እስከ 6ኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች ከ300 ሺህእስከ 100 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል።

በሰለሞን በቀለ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 16 ጎሎችን በማስቆጠር ሲሸልስን አሸነፈአዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሲሸልስ ጋር ባደረገው ዓለም አቀ...
30/09/2026

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 16 ጎሎችን በማስቆጠር ሲሸልስን አሸነፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሲሸልስ ጋር ባደረገው ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታ ሲሸልስን 16 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ረትቷል።

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ንግሥት በቀለ፣ ታሪኳ ዴቢሶ፣ እሙሽ ዳንኤል፣ አረጋሽ ካልሳ እና ቤተልሄም መንተሎ በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ምኅረት አየለ፣ እፀገነት ግርማ፣ ቱሪስት ለማ፣ ሚለን ጋይም፣ ዳግማዊት ሰለሞን እና ማህሌት ምትኩ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

የሀገራቱ ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታ ቅዳሜ መስከረም 23 ቀን 2019 ዓ.ም ይካሄዳል።

ቻለው ለሜቻ በሁለት ዓመት ውል የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆነው ባለፈው ሳምንት መሾማቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ ጋር የሁለተኛ ዙር የኦሎምፒክ የማጣሪያ ጨዋታዎቿን መስከረም መጨረሻ እና ጥቅምት ወር መግቢያ ላይ ታደርጋለች።

የወዳጅነት ጨዋታዎች የብሔራዊ ቡድኑ የማጣሪያ ዝግጅት አካል ናቸው።

ማንቼስተር ሲቲ በፕሪሚየር ሊጉ የፋይናንስ ሕጎች ጥሰት ጥፋተኛ ተባለአዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ሲቲ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የፋይናንስ ሕጎችን በከባድ ...
29/09/2026

ማንቼስተር ሲቲ በፕሪሚየር ሊጉ የፋይናንስ ሕጎች ጥሰት ጥፋተኛ ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ሲቲ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የፋይናንስ ሕጎችን በከባድ ሁኔታ በመጣስ በቀረቡበት በሁሉም ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን ሊጉ አስታውቋል።

ክለቡ ከ2009/10 እስከ 2017/18 የውድድር ዓመታት ያደረጋቸውን የንግድ ስምምነቶች በማዛባት ትክክለኛ ያልሆነ የገቢ መጠን እንዳሳየና የተሳሳተ የፋይናንስ መረጃ እንዳቀረበ የሊጉ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን በምርመራው ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ክለቡ የምርመራ ሂደቱን ለማደናቀፍ ሙከራ በማድረግ የትብብር ግዴታውን እንደጣሰ ነው የተገለጸው።

እንደ አጣሪ ኮሚሽኑ ግኝት፤ እነዚህ የፋይናንስ ህግ ጥሰቶች ከ900 ሚሊየን ፓውንድ በላይ የሚገመት ገቢና ወጪ እንዲዛባ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ ባወጣው መግለጫ ጉዳዩ በተጨማሪ ችሎት እንደሚታይ የገለጸ ሲሆን፤ በክለቡ ላይ የሚጣለውን ቅጣት በተመለከተ ውሳኔ አልተሰጠም፡፡

ሆኖም ክለቡ በገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽኑ የምርመራ ውጤት ላይ እስከመጪው አርብ ድረስ ይግባኝ የማለት መብት እንዳለው ተገልጿል፡፡

ሙሽራዋ ባህር ዳርአዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ ባሕር ዳር በተለመደው ውበቷ ብቻ አልነበረችም፤ በደስታ ተሞልታ፤ ሙሽራ ሆና ሙሽሮቿን አስተናግዳለች።የኢትዮጵያ እና...
29/09/2026

ሙሽራዋ ባህር ዳር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ ባሕር ዳር በተለመደው ውበቷ ብቻ አልነበረችም፤ በደስታ ተሞልታ፤ ሙሽራ ሆና ሙሽሮቿን አስተናግዳለች።

የኢትዮጵያ እና የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድኖች የዛሬ የባሕር ዳር ስታዲየም ጨዋታ፤ ከመጫወቻ ሜዳው አጥር በሚዘል የከተማዋ ልብ በደጋፊዎች ምት የመታበት ሆኖ ነው ያመሸው።

የስታዲየም መግቢያ ትኬት ለመቁረጥ ከሰዓታት በፊት የተሰለፈው ሕዝብ፣ የስታዲየሙን ዙሪያ የከበቡ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች፣ በሰንደቅ ዓላማና በማልያ ያጌጡ ወጣቶች፡ ሁሉም አንድ ነገር ይናገራሉ፤ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስን ይወዳሉ የሚለውን።

ዛሬ ሰው ቤቱ የቀረ አይመስልም፤ መንገዱ ሁሉ ያመራው ወደ ስታዲየም ነው።

እይታው ወደ ሜዳ ነበር፤ ልቡ ደግሞ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር፤ ምንም እንኳን ዋልያውን ውጤት ባይቀናውም።

በዚህ የስፖርት ድባብ ውስጥ ባሕር ዳርም የራሷን ታሪክ እየጻፈች መሆኑን አሳይታለች።

ሰላም በሚነፍስበት አየሯ፣ በተፈጥሮ ውበቷና በተለየ አቀባበሏ የምትታወቀው ባለዘንባባዋ ከተማ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትልልቅ ሀገራዊና አህጉራዊ መድረኮችን ለማስተናገድ የራሷን ቦታ እያጠናከረች ነው።

ጨዋታው ለከተማዋ የስፖርት ድምቀት ብቻ አይደለም፤ ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርት፣ ለንግድና ለቱሪዝም እንቅስቃሴም መነቃቃት የፈጠረ ነው።

የባሕር ዳር ስታዲየም ከዓመታት በኋላ የአህጉራዊ ጨዋታ መድረክ መሆኑም የከተማዋን የስፖርት ቱሪዝም አቅም የሚያሳይ ነው።

ይህም ከከተሞች ልማትና ለከተሞች ከሚሰጠው ትኩረት ጋር ሲታይ፤ ባሕር ዳር የምትገነባው መሠረተ ልማት ብቻ ሳይሆን የምትፈጥረው የመድረክ አቅምም ነው።

ከሐይቅ ዳርቻዋ እስከ ስታዲየሙ ዙሪያ ዛሬ ባሕር ዳር አንድ መልዕክት አስተላልፋለች፤ ይኸውም ከተማ ማለት ሕንፃና መንገድ ብቻ ሳይሆን፤ ሰዎችን የሚያሰባስብ፣ ታላላቅ መድረኮችን የሚያስተናግድና ታሪክን የሚፈጥር ሕያው መድረክ መሆኑን ነው።

ዛሬ ሙሽራዋ ባሕር ዳር ናት፤ ሙሽሮቿ ደግሞ የኢትዮጵያ እና የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድኖች።

እንግዶቿ የሺዎች የልብ ምት ናቸው፤ ስታዲየሟ ደግሞ የዛሬዋ ታሪክ መድረክ ነው።

ባሕር ዳር ዛሬ ጨዋታ ብቻ አላስተናገደችም፤ ፍቅርን፣ ደስታን፣ አብሮነትንና የአንድ ከተማን የመድረክ አቅም አሳይታለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሽንፈት አስተናገደአዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በሴኔጋል አቻው 1 ለ 0 ተሸንፏል፡፡ዋሊያዎቹ...
29/09/2026

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሽንፈት አስተናገደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በሴኔጋል አቻው 1 ለ 0 ተሸንፏል፡፡

ዋሊያዎቹ በባህር ዳር ስታዲየም ከሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር ባደረጉት የ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ 2ኛ ጨዋታ ድል አልቀናቸውም፡፡

በጨዋታው ኢብራሂም ምባዬ በ11ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አሸንፏል፡፡

በዚሁ ምድብ ሞዛምቢክ ሱዳንን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ያሸነፈች ሲሆን፤ ከሴኔጋል ከግብ ክፍያ በመብለጥ ምድቡን በ4 ነጥብ መምራት ጀምራለች፡፡

ኢትዮጵያ 0 – 1 ሴኔጋል ፡ የመጀመሪያ አጋማሽ ውጤትአዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን 1 ለ 0 እየተመራ የመጀመሪያውን ...
29/09/2026

ኢትዮጵያ 0 – 1 ሴኔጋል ፡ የመጀመሪያ አጋማሽ ውጤት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን 1 ለ 0 እየተመራ የመጀመሪያውን አጋማሽ አጠናቅቋል፡፡

ዋሊያዎቹ ለ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ከሴኔጋል አቻቸው ጋር የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በባህርዳር ስታዲየም እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በጨዋታው ኢብራሂም ምባዬ 11ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ በሴኔጋል መሪነት ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ሴኔጋልን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቋሚ አሰላለፍ ይፋ ሆነአዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሴኔጋል...
29/09/2026

ሴኔጋልን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቋሚ አሰላለፍ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሴኔጋል አቻው ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ከደቂቃዎች በኋላ በባህር ዳር ስታዲየም ይጀመራል፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ሴኔጋልን የሚገጥመውን የዋሊያዎቹ ቋሚ አሰላለፍ ይፋ አድርገዋል፡፡

በዚህም መሰረት፡- አቡበከር ኑራ፣ ብርሃኑ በቀለ፣ በረከት ሳሙኤል፣ ያሬድ ባዬ፣ ሳሙኤል ዮሃንስ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ ቢኒያም ፍቅሩ፣ አቤል ያለው እና ቸርነት ጉግሳ በቋሚ አሰላለፍ ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡

በተመሳሳይ በሴኔጋል በኩል፡- ይሄቫን ዲዩፍ፣ ሙሳ ኒካቴ፣ ሳዳቡ ሳኔ፣ ማላንግ ሳር፣ ኤልሃጂ ማሊክ ዲዩፍ፣ ላሚን ካማራ፣ ፔፔ ጉዬ፣ አሳን ዲያዮ፣ አብዱላህ ሲማ፣ ኢብራሂም ምባዬ፣ ኒኮላስ ጃክሰን በቋሚ አሰላለፉ ተካትተዋል፡፡

ሰዒድ ሀብታሙ፣ ፍሬው ጌታሁን፣ ርሆቦት ሳላሎ፣ ራምኬል ጀምስ፣ ሀብታሙ ጉልላት፣ ቢኒያም በልዬ፣ ፍጹም ጥላሁን፣ ዳዋ ሁቴሳ፣ አብዱሰላም የሱፍ እንዲሁም ካርሎስ ዳምጠው በተጠባባቂነት በዋሊያዎቹ ስብስብ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ዋሊያዎቹን ከስደት የመለሰው የባህርዳር ስታዲየምአዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ዋንጫ መስራች የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ለበርካታ አስርት ዓመታት በእግር ኳሱ በውጤ...
29/09/2026

ዋሊያዎቹን ከስደት የመለሰው የባህርዳር ስታዲየም

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ዋንጫ መስራች የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ለበርካታ አስርት ዓመታት በእግር ኳሱ በውጤት ማጣት ውስጥ ቆይታለች፡፡

ከፍተኛ የእግር ኳስ ፍቅር ያለው ሕዝቧም ለዓመታት በብሔራዊ ቡድኑ ጮቤ የሚያስረግጥ ድል ለማጣጣም አልታደለም፤ ብሔራዊ ቡድኑን በስታዲየም ተገኝቶ ለመደገፍም እድሉን ሳያገኝ ቆይቷል፡፡

ዋሊያዎቹ ለዓመታት የአፍሪካ ዋንጫና የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎችን በሀገራቸውና በደጋፊዎቻቸው ፊት ለማድረግ የሚያስችል ስታዲየም በማጣታቸው "ስደተኛው ብሔራዊ ቡድን" እስከመባል ደርሰዋል፡፡

ዛሬ ግን ዋሊያዎቹ ከስደት ተመልሰዋል፤ ኢትዮጵያውያንም የሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ አድርገው ብሔራዊ ቡድናቸውን ሊደግፉ በባሕር ዳር ስታዲየም ዙሪያ ተሰብስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ የሚያስችል ሰፋፊ የስታዲየም ግንባታና የስፖርት ልማት ስራዎችን በትኩረት እያከናወነች ትገኛለች፡፡

ከእነዚህ ጥረቶች መካከል ባለፉት ዓመታት የባህርዳር ስታዲየምን ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ይጠቀሳሉ፡፡

የባህርዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ የተሰሩ ስራዎች ፍሬ አፍርተው፤ ስታዲየሙ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ዝቅተኛ መስፈርቶችን በማሟላቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ከስደት መመለስ ችሏል፡፡

ከከታንዛንያው ቤንጃሚን ምካፓ እና ከሩዋንዳው አማሆሮ እስከ ሞሮኮው ኤል አብዲ ስታዲየም፣ ከቡርኪና ፋሶ ስታድ ዱ ፎር እስከ ኮትዲቯር ስታድ ደ ኢቢምፔ ዋሊያዎቹ ስታዲየም ፍለጋ ያልኳተኑበት የለም፡፡

ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች አለመኖራቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ማጣት አንዱና ዋነኛው ምክንያት መሆኑን የስፖርት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ለዚህ ችግር ምላሽ ለመስጠት መንግሥት የስፖርት ልማት ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባህርዳር ስታዲየም በተለያዩ ጊዜያት ባደረጓቸው ምልከታዎች፤ ስታዲየሙ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ማስተናገድ እንዲችል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡

በጥቂት ወራት ውስጥመረ ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስናገድ እንደሚጀምር የሰጡት ቃል ወደ ተግባር ተቀይሮ፤ በዛሬው እለት ዋሊያዎቹ ከቴራንጋ አናብስት ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ለማስተናገድ ዝግጁ ሆኗል፡፡

በዚህም ለዓመታት ስደተኛ የነበረውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ሀገሩ እንዲሁም እግር ኳስ አፍቃሪውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ስታዲየም በመመለስ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ቀን 10 ሰዓት ላይ ይጀምራል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Address

Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when FMC Sport posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share