
17/03/2025
የአፋርና ሶማሌ ሕዝብን አብሮነት ለማጠናከር በትብብር መስራት ይገባል- ሼኽ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋርና የሶማሌ ሕዝብን አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር በትብብር መስራት ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ።
የአፋር እና ሶማሌ ወንድም ሕዝብ የጋራ ኢፍጣር መርሐ ግብር በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተካሂዷል።
ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በዚህ ወቅት፥ ረመዳን የአንድነት፣ የመተሳሰብ እና የመተጋገዝ ወር መሆኑን አውስተዋል።
ይሄን ታላቅ የወንድማማቾች የፍቅርና የመተሳሰብ ኢፍጣር ከአመራሮቹ አልፎ በሕዝቦች ዘንድ እርቅና ሠላምን ለማስረጽ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል ።
በቀጣይም የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነትና ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክሩ የልማትና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን በትኩረት ማከናወን ይገባል ነው ያሉት።
በተያዘው ረመዳን ወር በሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እየተጉ ያሉ አካላትን አመስግነዋል።
የሰላም ሚኒስትር መሐመድ ኢድሪሰ በበኩላቸው ÷ ሁለቱ ክልሎች ተቀራርበው ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የሁለቱ ክልል ሕዝቦች በርካታ የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመው÷ይህን ትስስር ለማጠናከርና ወንድማማችነትን ለማጉላት የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የሠላም፣ የእርቅ፣ የፍቅር ወር በሆነው የረመዳን ወር ምሽት በተካሄደው የሠመራ የጋራ ኢፍጣር ላይ የሁለቱ ክልል አመራሮች ዳግም ግጭት ውስጥ ላለመግባት ቃል ገብተዋል።