19/06/2025
የዜና እርማት ስለመስጠት
ድሬ ቲዩብ ሰኔ 11 ቀን 2017 "የራሳቸው ቆጣሪ ሳይኖራቸው ከጎረቤት በገመድ ኃይል ስበው በሚገለገሉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ ቅጣት እንደሚጣል ተገለጸ" በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ዋቢ በማድረግ ዘገባ አሠራጭቷል።
ይሁንና አዲስ በፀደቀው መመርያ አንቀፅ 2.3.2 ቅጣቱ የሚጣልበት የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት መፈጸሙ ለተረጋገጠበት ደንበኛ መሆኑን ተገንዝበናል። ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እየጠየቅን ቅጣቱ የሚጣለው ስርቆቱን ከአቅርቦት መነሻ ለፈፀመ መሆኑ ተስተካክሎ እንዲነበብ ለመጠየቅ እንወዳለን።
ስርቆቱን የሚፈፅም ደንበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ በጊዜያዊነት ከምሰሶ ወይም ከአቅርቦት መነሻ ላይ የሚቋረጥ ሆኖ የድርጅቱ የሕግ አገልግሎት ፖሊስ ወይም የህግ አካል የምርመራ ሒደቱን ማጠናቀቁን በጽሑፍ እስኪያሳውቅ እንዲሁም ደንበኛው የሚጠበቅበትን ክፍያ እስኪፈፅም እና መተማመኛ የውል ሠነድ ላይ እስኪፈርም ድረስ ተቋርጦ የሚቆይ ይሆናል፡፡ ሲስተም ላይ በጊዜያዊነት ተቋርጦ የሚቆይ ሆኖ ውሳኔ ካገኘ በኋለ ቀጣይ ርምጃ ይወሰዳል፡፡
በተጨማሪም ማቋረጡ እና ጥፋቱ ለሕግ አገልግሎት ክፍል ማስተላለፉ እንዲሁም የጥፋቱ መረጃ ፋይል መደረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሌሎች ክፍያ በተጨማሪ ውል በመተላለፉ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመካከለኛ ኢንዱስትሪ ታሪፍ መደብ ተጠቃሚ ብር 1,000,000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር)፣ ለዝቅተኛ ኢንዱስትሪ ታሪፍ መደብ ተጠቃሚ ብር 750,000.00 (ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር)፣ ለጠቅላላ ታሪፍ መደብ ተጠቃሚ ብር 500,000.00 (አምስት መቶ ሺህ ብር) እና ለመኖሪያ ቤት ታሪፍ መደብ ተጠቃሚ ብር 20,000.00 (ሃያ ሺህ ብር) ቅጣት ይጣላል።
ከዚህ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርቆት በድጋሚ መፈጸሙ ለተረጋገጠ ደንበኛ ቀድሞ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ አስተዳደራዊ ቅጣቱ ሁለት እጥፍ እንዲከፍል ይደረጋል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ከመኖሪያ ቤት ታሪፍ መደብ ተጠቃሚ በቀር ለጠቅላላ ታሪፍ ደንበኛ 1 ሚሊዮን ብር፣ ለዝቅተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ታሪፍ ደንበኞች ደግሞ 2 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ (Security Deposit) ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያስይዝ ይደረጋል፡፡
ከሁለት ጊዜ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት ለሚፈጽም ደንበኛ ከላይ የተቀመጠው እንደተጠበቀ ሆኖ አስተዳደራዊ ቅጣቱና ተቀማጩ (Security Deposit) ቀደም ሲል ከከፈለው በእጥፍ እንዲያሳድግ ይደረጋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት ፈጽሞና በአሠራር ሥርዐቱ መሠረት ተገቢውን መስፈርት አሟልቶ ኃይል የተገናኘለት ደንበኛ ለሁለት ዓመት በሕጋዊ አግባብ መጠቀሙ ሲረጋገጥ ያስያዘው ተቀማጭ (Security Deposit) ገንዘብ እንዲመለስለት የሚደረግ ይሆናል።
#ድሬቲዩብ