
29/08/2025
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ወቅታዊ መረጃ።
ሀሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን በመጠቀም ህዝብን ከህዝብ ጋር፣ ህዝብን ከመንግስት ጋር ለማጋጨት እና ከሌሎች የአገራችንና የክልላችን ሰላም ለማናጋት በውስጥና በውጭ ከምንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በትስስር በመሥራት የተጠረጠሩ 9 ግለሰቦችን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ማጣራት ጀምሯል፡፡
እነዚህ ተጠርጣሪዎች ማንነታችን አይታወቅም በሚል የክልሉን ህዝብ ስላምና ለዘመናት የቆየ አብሮነት እንዲሸረሸርና ጥርጣሬ እንዲፈጠር ምንም መሠረት የሌላቸውን ሀሰተኛ መረጃዎች በማሰራጨት ለዚሁ ተግባራቸው ከጀርባቸው ሆነው ጥቅም የሚሰጧቸውን ጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ለማሳካት ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው፡፡
ተጠርጣሪዎች የጥላቻ ንግግርን፣ ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭት እና ስም የማጥፋት እኩይ ሥራ እንደ አንድ የገቢ ማግኛ ምንጭ አድርገው እየተጠቀሙ ቆይተዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ህግ በማስከበር የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በማንኛውም በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን በህግ ቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ የማጣራት ሥራውን አጠናክሮ የሚቀጥል ስለሆነ ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎችን በሀሳብና በገንዘብ በመደገፍ የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት ከጀርባ ሆነው የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
በዚህ አጋጣሚ የእነዚህን ግለሰቦች መሠረተ-ቢስ መረጃ በመቃወምና የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ የክልሉ ፖሊስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ መረጃ በመስጠት ከፍተኛ ትብብር የሚያደርጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን እያመሰገነ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ፖሊስ እየወሰደ ያለውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያሳውቃል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን
ነሐሴ 23 ቀን 2017 ዓ/ም
ላስካ