
05/09/2025
ምሁራንን በማስተባበር ሀገር የያዘችውን የለውጥ ጉዞ ማሳካት እንደሚቻል የኮንሶ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
አርባምንጭ ነሐሴ 30 ፣2017ዓ.ም (ኤፍኤም 90.9)
የኮንሶ ምሁራን ማህበር "ላስተማረኝ ማህበረሰብ ምን ላድርግ?" በሚል መሪ ቃል 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የኮንሶ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጉራሾ ጎስኬ፣ ምሁራን የአገሪቱን የለውጥ ጉዞ በማገዝ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚንሸራሸሩ አሉታዊ መልዕክቶች እንዲወገዙ እና ምሁራን የእድገት እንቅፋት ከሆኑ ነገሮች እንዲርቁ አሳስበዋል።
የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ ኩማቾ ኩሴ፣ ምሁራን ለተማሩበት ማህበረሰብ የሚበጅ ነገር እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አማኑኤል ኩሲያ ፤ ማህበሩ የተለያዩ ችግር ፈቺ ጥናቶችንና ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ እንዲሁም ከኮንሶ እስከ አሜሪካ ባሉ ቅርንጫፎች ውስጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከንግግር ባሻገር የሀገርቱንና የኮንሶን አንድነት ለማጎልበት፣ በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ተግባራዊ መፍትሄዎችን ለመፍጠር፣ ለሰላም ግንባታ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ሀሳቦች ቀርበዋል።
የኮንሶን እርከኖች ለመስራት ትጋትና ትዕግስት እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ፣ ምሁራንም የሚመኙትን የተለወጠ እና የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር በጽናትና በትብብር መስራት እንዳለባቸው ተገልጿል።
በመጨረሻም "ሰላም ይቀድም"፣ "ተባብረን እንጓዝ" የሚሉ መርሆች ተንጸባርቀዋል።
በጉባኤው የተገኙ አባላትም ለህብረተሰባቸው በትጋት ለመስራት እና ከአጎራባች ዞኖች ምሁራን ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
ዘጋቢ ፡የአማሮ አርሳባ