24/04/2025
#የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ #አቶ ጴጥሮስ ወ/ማሪያም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል አስመልክተዉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የተከበራችሁ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ2017 ዓ.ም ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!
የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ መታሰቢያ በዓል አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ የተነሳበት የአሸናፊነት ማሳያ ነዉ።
የትንሳኤ በዓል ፈተናዎችን በፅናትና በትጋት በማለፍ ዳግም ማንሰራራት እንደምንችል የሚያመላክት ታላቅ የተስፋ ምልክት እና ሰብአዊነትንና ልግስናን፣ ቸርነትንና በጎነትን፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖርንና ይቅርታን፣ ምህረትንና ደግነትን ያስተምራል።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው ለሰው ልጆች ለመዳን የከፈለዉን ታላቅ የደም ዋጋ የሚያሳይ በመሆኑ አርአያነቱን ተከትለን በየፈርጃችን የሚስተዋሉብንን ድክመቶቻችንና ውስንነቶቻችንን በማረም ለላቀ ህዝብ ተጠቃሚነት ተግተን መስራት ይጠበቅብናል፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን እያገጠሙን ያሉንን ጊዜያዊ ፈተናዎችን በአሸናፊነት ለማለፍ በላቀ የትብብር መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
ብዙ ከተቀበለ ብዙ ይጠበቃል! ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን በመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጥቶ የፍቅሩን ጥልቀት ካሳየን ዛሬ በሀገራችን የተዘራዉን የጥላቻና የከፋፋይ አጀንዳን በመድፈቅ ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነት እሴትን ማጎልበት ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ በህብር ያገጠች የብዝሃ ሀይማኖት፣ ባህልና ቋንቋ ባለቤት ናት።
በመሆኑም ይህንን ታላቅ ዕሴት በመጠበቅና በመንከባከብ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብን፣ ከመገፋፋት፣ መደጋገፍንና መተባበርን በማጎልበት ሀገራዊ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ህይወትን ስላካፈለን እኛም ፈለጉን በመከተል በዓሉን ስናከብር አቅመ ደካሞችን በመንከባከብ፣ የታረዙትን በማልበስና የተራቡትን በማብላት፣ የታመሙትን በመጠየቅና በህግ ጥላ ስር ያሉ ወገኖችን በመጎብኘት እንድታከብሩ አሳስባለሁ።
መልካም የትንሣኤ በዓል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!