01/11/2025
የቦሮ ህዝቦች ታሪክና ትውፊት ላይ መሰረት ያደረገ በደራሲ አመንቴ ገሺ የተሰናዳ “ቦር-ዘኢትዮጵያ” የተሰኘ መፅሐፍ በአሶሳ ከተማ ተመረቀ፡፡
በምርቃ ስነ-ስርዓቱ የቦሮ ሽናሻ ልማት ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገብረሚካኤል ጉድሬ እንዳሉት “ቦር-ዘኢትዮጵያ” የተሰኘ መፅሐፍ የቦሮ ህዝቦች የረጅም ዘመን ታሪክና ትውፊትን የሚያወሳ የምርምር ሰነድ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ታሪክን በትክልል ሰንዶ ለትውልድ ማሳወቅ፣ ማስቀመጥና ማስተላለፍ ለአንድ ህዝብ ብሎም ለሀገር ያለው አበርክቶው የላቀ መሆኑን ገልፀው የመፅሐፉ ደራሲ አመንቴ በቀጣይ መሰል የምርምር ስራዎችን ለሚሰሩ አካላት ስንቅ ይሆናቸዋልም ብለዋል፡፡
የመፅሐፉ ደራሲ አመንቴ ገሺ እንደሚሉት የቦር-ዘኢትዮጵያ መፅሐፍ ዓመታትን የጠየቀ የምርምር ስራ ውጤት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በታሪክ ሰነዶች እና በተለያዩ መዛግብቶች ፍተሻና ከብሔረሰቡ ታላላቅ አባቶች ጋር በተደረገ ቃለ-መጠይቅን መነሻ አድርጎ የተሰናደ የምርምር ሰነድ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ይህ በቦሮ ህዝቦች ላይ የሚያተኩረው የታሪክና የትውፊት መፅሐፍ የምርምር ሂደቱ ቀጣይነት ባላቸው ሁለት ቅፆች ምሉዕነቱ እንደሚረጋገጥም ፀሐፊው ጠቁመዋል፡፡
ለመፅሐፉ እውን መሆን አበርክቶ ለነበራቸው አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመፅሐፉ ዙሪያ ዳሰሳዊ እይታቸውን ያቀረቡ አካላት በበኩላቸው ደራሲው ያካሄደው ዓመታትን የተሻገረ የምርምር ሂደት የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ታሪካዊና ትውፊታዊ ሰነዱ በቀጣይ መሰል ስራዎችን ለሚሰሩ አካላት መነሻ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡
በቦሮ ህዝቦች ዘንድ የነበረውን በታሪክ ተውልዱ በልኩ እንዲያውቅ የሚያስችል ሰነድ ነው ያሉት ደግሞ የመፅሐፉ ምርቃ ስነ-ስርዓቱ ታዳሚያን ናቸው፡፡
መፅሐፉ በ288 ገፆች የተከተበ ሲሆን በ4 መቶ 95 ብር ገበያ ላይ ውሏል፡፡