
12/08/2025
የሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ ውድቀትና የቁልቁለት ጉዞ ማን ነው ተጠያቂው?!
አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስን የቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ የሾመው የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ለዳሞ የመጀመሪያ ተጠያቂ ናቸው። ሰለ ስፖርት ግንዛቤ የለሌውንና በወንጀል የተጨመላለቀውን ሰው አምጥቶ የሲዳማ ቡና ቦርድ አመራር ሰብሳቢ አድርጎው በመሾሙ ለሲዳማ ህዝብ ሀፍረት ቀዳሚ ተጠያቂ ነው። ሁለተኛ ተጠያቂ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ ነው። አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ በወቅቱ ባደረጃው የፖለቲካ ጡንቻ እያስፈራራ፣ የደጋፊዎችን ጬሄት በገንዘብ እየገዛ ክለቡን ከስፖርት ህግ ውጭ በጡንቻ እየመራ መቀመቅ በመክተቱ ሁለተኛ ተጠያቂ ነው።
በሦስተኛ ደረጃ ያለው የሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ የቦርድ አመራሮች ናቸው። በተለይም በተጨዋቾች ግዥ ወቅት የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ከአንድ ተጨዋች ከ1-4 ሚሊዮን ብር ፈርቅ በመያዝ ግዥ የፈፀሙ (አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ፣ አቶ ፍሬው አሬራ፣ አቶ ወሰንየለህ፣ ዶ.ር ዳዊት ሀዬሶ እና ከደጋፊዎች ማህበር አቶ ደጀነ ማርቆስ) ዋነኛ ተጠያቂዎች ናቸው። ከእነሱ ባሻገር የተጨዋቾች ግዥ ውሳኔ ያፀደቁ የቦርድ አመራሮች በሙሉ ለሲዳማ ቡና ውድቀትና ለሲዳማ ህዝብ ውርደት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ።
በአራተኛ ደረጃ የክለቡ ሥራ አስክያጅና ኮችንግ ስታፍ ተጠያቂ ናቸው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እገዳ ኪሣራም ቢሆን ገንዘብ ከፍሎ የሲዳማን ህዝብ ክብር መጠበቅ እየቻሉ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ይዞ በመሄድ፣ የታገዱ ተጨዋቾችን በማሰለፍ፣ ቢያንስ ለኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ እንኳን አንድም የቅጣት ገንዘቡን ከፍለው የታገዱ ተጨዋ ማሰለፍ ወይም የታገዱ ተጨዋቾችን ባለማሰለፍ የክለቡን ጥቅምና የህዝቡን ክብር መጠበቅ እየቻሉ ሆን ብለው በማሰለፋቸው ክለቡን ጎድተዋሉ። የሲዳማን ህዝብ አዋርደዋሉና ተጠያቂ ናቸው።
በአምስተኛ ደረጃ ይህ ሁሉ የሕግ ጥሰት እያለ ብለው ህዝብንና መንግሥትን ያሳቱ የክለቡን የውስጥ ውስጡን ጉዳይ የሚያውቁ የክለቡ አመራሮች በሙሉ ለዋንጫ አቀባበል ለባከነው ሀብትና ጉልበት፣ ደጋፊውና ሰፊው ህዝብ በአቀባበል ሥርዓቱ ለገጠመው ሀፍረት ተጠያቂ ናቸው።
ስድስተኛ በሕግ አግባብ ውጭ የተገዙ ተጨዋቾችም ክለቡ ለገጠመው ኪሣራና ያለአግባብ ለጎደፈው ሰፊው የሲዳማ ህዝብ ክብርና ስም ተጠያቂ ናቸው። ከሕግ አግባብ ውጭ እንደፈረሙ እያወቁ የተቀበሉትን ገንዘብ የክለቡን ጥቅምና የህዝቡን ክብር በጠበቀ መልኩ መያዝ ሲገባቸው በእንዝላልነት በመያዝ ከለቡን ለውስብሰብ ችግር በመዳረግ ለሲዳማ ህዝብ ውርደት ምክንያት በመሆናቸው ከተጠያቂነት አያመልጡም።
በሰባተኛ ደረጃ በዚህ ሁሉ ሂደት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የሊግ ካምፓኒው በሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ ላይ የፈፀሙትን የሕግ ጥሰትና የአሠራር ክፍተት በመጥቀስ ጉዳዩን በCAS በዘርፉ እውቀትና ጥበብ በተካኑ ባለሙያዎች በመምራት የክለቡን ክብርና የሲዳማን ህዝብ ክብር መጠበቅ እየተቻለ አቤቱታ እንኳን በአግባቡ ማቅረብ ባለመቻል ጉዳዩ ከጅምሩ ውድቅ እንዲሆን ያደረጉ አመራሮችና አካላት የህዝብንና የመንግሥትን ሞራል መጠበቅ የሚያስችል ሌላ እድል ያመከኑ በመሆናቸው ተጠያቂነት አለባቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብና የሊግ ካምፓኒው በአራቱ ክለቦች ላይ ብቻ ምርመራ አድርገው ያሳለፉት አድሎአዊ ውሳኔ እንዳለ ሆኖ የሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ በታገዱ የቦርድ አመራሮች እየተመራ የታገዱ ተጨዋቾች እያጫዎተ ዓመቱን ሙሉ ዝምታ መርጠው ማስተካከያና የእርምት እርምጃ መውሰድ በማይቻልበትና ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ዋንጫ አጨብጭበው ሰጥተው ህዝቡ ደስታውን ገልፆ ለዋንጫው ጮቤ ረግጦ አቀባበል ካደረገ ቦኋላ ያስተላለፉት ውሳኔ በእግር ኳስ ዓለም እጅጉን የሚያሳፍር ከመሆኑም በላይ ለሰፊው የሲዳማ ህዝብ ፌዴሬሽኑ ያለውን ንቀት የሚያሳይ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ የታሪክ ተጠያቂ ነው።
Luwa Media