
30/07/2025
!
ፈጣሪ ስላንተ ሁሉንም ነገር ቢያውቅም ከዚህ በላይ አይገባህም ብሎ ግን አልወሰነም። የመረጥከውን ህይወት እንድትኖር ነፃነቱን ሰቶሃል። ሙሉ ዘመንህን በመካከለኛነት /average/ ደረጃ ማሳለፍ ወይም ለትንሽ ጊዜ ዝቅ ብለህ ቀሪው ዘመንህን በከፍታው ማሳለፍ ያንተ ምንጫ ነው። በጣርከውና በለፋሀው ልክ ታገኛለህ፤ የሚገባህም ይሰጥሃል። ምናልባት ከዚህ በፊት እንደ ልፋትህ አልተከፈለህ ይሆናል፤ አንተ ደክመህ ሌላው ተጠቅሞ ይሆናል፤ አንተ ታግለህ ሌላው አሸንፎ ይሆናል። ነገር ግን ሁሌም እንደዛ አይሆንም፤ በፅናትህ ልክ የተሻለ ጊዜ ይመጣል፤ እንደ ትዕግስትህም ያሰብከውን ታገኛለህ።
ቀጣዩን ምዕራፍ እመነው! ምክንያቱም ደራሲው አንተ ነህና። ለቀደመው ምዕራፍ መበላሸት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂው አንተ ላትሆን ትችላለህ፤ ለእራስህ ህይወት ድርሰት ግን ተጠያቂነት ሊሰማህ ይገባል። ደራሲና ዋና ተዋናይ በሆንክበት የእራስህ ድርሰት የጉዳዩ ወሳኝና ባለቤት አንተ ነህ፤ ጭብጡን የምታስተካክለው፤ መቼቱን የምትመርጠው፤ ረዳት ተዋናይን የምትመድበው አንተ ነህ። ስለዚህ ባንተ ምክንያት ለሚከሰተው እያንዳዱ ነገር ሃላፊነት ውሰድ፤ ስህተትህን ተቀበል፤ በቀጣይ ምዕራፍ ለማስተካከል ተዘጋጅ።