
01/05/2025
እስራኤል ያጋጠማትን ሰደድ እሳት ተከትሎ የዓለምአቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ ጠየቀች
*********************
እስራኤል በእየሩሳሌም ከተማ አቅራቢያ ያጋጠማትን ከባድ ሰደድ እሳት ተከትሎ የዓለምአቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ ጠይቃለች፡፡
ከእየሩሳሌም በቅርብ ርቀት ላይ የተከሰተው ከባድ ሰደድ እሳት መዛመቱን ተከትሎ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም በሰደድ እሳቱ የተነሳ በርካታ መንገዶች እንዲዘጉ መደረጉም ተነግሯል፡፡
ባለው ከባድ የአየር ጠባይ እና በኃይለኛ ንፋስ ታግዞ እየተዛመተ የሚገኘውን የሰደድ እሳት ለመቆጣጠር የእሳት አደጋ ሰራተኞች ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ሃገሪቱ ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ ላይ መሆኗን ገልፆ፤ የሰደድ እሳቱን ለመከላከል የዓለምአቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ ጠይቋል፡፡
የተከሰተው የሰደድ እሳት ምናልባትም በታሪክ ትልቅ የሚባል መሆኑን የገለጹት የእየሩሳሌም ግዛት የእሳት አደጋ ድፓርትመንት ኮማንደር ሽሙሊክ ፍሬይድማን፤ የሰደድ እሳቱ በሰዓት 60 ማይል ፍጥነት የሚጓዝ በመሆኑ የበለጠ እንዳይዛመት አስጊ አድርጎታል ብለዋል፡፡
የሰደድ እሳቱ በኃይል መዛመቱን ተከትሎ ባለስልጣናቱ ቴላቭቭን ከእየሩሳሌም የሚያገናኘውን መንገድ ለመዝጋት መወሰናቸውንም ነው የተገለጸው፡፡
በእስራኤል እሮብ እለት የተከሰተውን የሰደድ እሳት ለመከላከል ሃገሪቱ ባቀረበችው የድጋፍ ጥያቄ 3 የእሳት መከላከያ አውሮፕላኖችን ከጣሊያን ማግኘቷም ተነግሯል፡፡