19/09/2025
የስልጤን ማህበረሰብ ትልቅነት በወራቤ ከፍታ ሰማይ ስር የማየት ህልም!!
ከወራቤ ከተማ አስተዳደር የተላለፈ መልዕክት!
አሰላሙ ዓለይኩሙ ወረሕመቱላሂ ወበረካቱሁ።
የሰላም ሰገነቷ ወራቤ ከተማ የስልጤ ህዝብ የአስተዳደሩ መዲና የትግሉ ፍሬ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የማህበራዊ ክላስተር ቢሮዎች መቀመጫ ከተማ ስትሆን በምቹ ተፈጥሯዊ አቀማመጥና የአየር ፀባይ የታደለችና በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ ሰፊ ከተማ ናት።
ውድ የስልጤ ወንድሞችና እህቶቻችን የጋራ ቤታችን ወደሆነችው የሰላም ሰገነቷ ወራቤ ከተማ እንኳን በደህና መጣችሁ።
እንደሚታወቀው የዞናችን ርዕሰ መዲና በሆነችው ወራቤ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በጀት የሚጠይቅ ትልቅ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ተግባር ተገብቷል።
ታዲያ ይህንኑ ታላቅ ፕሮጀክት ለማቀላጠፍ የከተማው፣ የዞኑና የወረዳዎች አመራሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ሌሎች አካላት የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛል።
እየተደረገ ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍም የወራቤ ከተማ አስተዳደር ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል።
ሰሞኑን በዞኑ በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ስር በሚገኙ ቀበሌዎች ለዚሁ የመንገድ ግንባታ ድጋፍ ይሆን ዘንድ በቁጥር በርካታ የሰንጋ አሰባሰብ ተደርጓል።
ለዚህም ከየወረዳው ሰንጋውን ለማስረከብ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ወራቤ ከተማ ቅድመ-ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁሉም የስልጤ ማህበረሰብ የተሰበሰበውን የሰንጋ ጎርፍ የሚረከብና ለሽያጭ የሚያቀርብ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ ገብቷል።
በመሆኑም በወራቤ ከተማ፣ በዙሪያው ያሉ ወረዳዎችና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ነጋዴዎችና የሆቴሎች ባለቤቶች ወደ ተዋቀረው ኮሚቴ ጋር በመቅረብ የተዘጋጀውን ሰንጋ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምቱና የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።
ከዚህ በተጨማሪም ከሳምንት በኋላ የመስቀል በዓል እንደሚከበር ይታወቃል። ለዚሁ በዓል እንኳን አደረሳችሁ እያልን በዚሁ አጋጣሚ በተመጣጣኝ ዋጋ ከተዘጋጀው ሰንጋ እንዲሸምቱ መልዕክት ተላልፏል።
የወራቤ ከተማ አስተዳደር
መስከረም 9፣ 2018 [ወራቤ ኮሙኒኬሽን]