
21/07/2025
በ2017 ዓ.ም ከ36 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 252 ባለሃብቶች ፈቃድ መስጠቱን የደብረ ብርሃን ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ
ደብረ ብርሃን፤ሀምሌ 14/2017 (ደብመኮ):- መምሪያው የ2017 ዓ.ም አፈፃጸም ግምገማ እና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ ትውውቅ መድረክ እያካሄደ ነው።
የደብረ ብርሃን ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረህይወት እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ200 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ 36 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 252 ባለሃብቶች ፈቃድ መሠጠቱን አስታውቀዋል።
ከነዚህ ውስጥ ለ55 ባለ ሃብቶች ከ70 ሄክታር በላይ መሬት መሠጠቱን ገልጸው ሁሉም ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ሲገቡ ከ21 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም አመልክተዋል።
በተያያዘም በ2017 ዓ.ም 16 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርት ለማሸጋገር ታቅዶ ለ5 ሺህ 200 ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ 25 አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርት ሥራ ማስገባት መቻሉን አስረድተዋል።
እንዲሁም ከ58 በላይ ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርት ማምረት መቻላቸውን እና 8 ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ለውጭ ገበያ ምርታቸውን መላካቸውን ነው ኃላፊ ያብራሩት።
የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ልማት ለተከታታይ 3 ዓመት በክልል ደረጃ አንደኛ በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ መኾን መቻሉን ጠቅሰው ለዚህ ስኬት እንዲበቃ በትጋት ለሠሩ የሥራ ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን አመስግነዋል።
የ2017 በጀት ዓመት አፈፃጸምና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ አቶ ብርሃን አቅርበዋል።