09/01/2026
«ጠላትህ ሰውየው አይደለም፣ አስተሳሰቡ ነው! - የሰለጠነ ልዩነት» 🤝🧠⚖️
********************************************
//እስቲ ራሳችንን በታማኝነት እንጠይቅ... በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት የልጅነት ጓደኛችሁን አጣላችሁ ታውቃላችሁ? ወንድም ወንድሙን "ብሎክ" (Block) ሲያደርግ አይተናል?
በሀገራችን የተፈጠረው ትልቁ ችግር፣ ልዩነትን እንደ ጠላትነት መቁጠር ነው።
"የእኔን ሀሳብ ካልደገፍክ፣ አንተ የሀገር ጠላት ነህ!" የሚለው አስተሳሰብ፣ ውይይቱን ገደለና ድንጋይ አሰነሳን።
ግን እኮ ፖለቲካ ማለት "የገበያ ቦታ" ነው። ገበያ ላይ ነጋዴዎች "የእኔ ይበልጣል፣ አይ የኔ ይሻላል" ብለው ይወዳደራሉ እንጂ፣ አይገዳደሉም። ሸማቹ (ህዝቡ) የወደደውን ይመርጣል።
የሰለጠነ ፖለቲካ (Civil Discourse) መርሆች፦
* ተቀናቃኝ እንጂ ጠላት አይደለንም!
በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ሁለት ቡድኖች ይፎካከራሉ። አንዱ ለማሸነፍ ሲሮጥ ሌላው ለመጣል ይሮጣል። ነገር ግን ጨዋታው ሲያልቅ፣ ማሊያ ተለዋውጠው ይጨባበጣሉ። ለምን? ተጋጣሚዎች እንጂ ጠላቶች ስላልሆኑ። በፖለቲካም፣ ሁላችንም የምንፈልገው "የኢትዮጵያን እድገት" ነው። መንገዳችን ይለያይ ይሆናል፤ ግባችን ግን አንድ ነው። የተለየ ሀሳብ ያለው ሰው፣ ሌላ አማራጭ ያቀረበ "ወንድም" እንጂ፣ ሊጠፋ የሚገባው "ቫይረስ" አይደለም።
* ሀሳቡን ንካ፣ ሰውየውን አክብር!
አንድ ሰው የተናገረው ሀሳብ ካልመቻችሁ፣ ሀሳቡን በምክንያት "ቦጭቁት"፤ ስህተቱን አሳዩ። ሰውየውን ግን አትሳደቡ።
"አንተ ደደብ ነህ" ማለት ስድብ ነው።
"ይህ ያነሳኸው ሀሳብ በዚህ ምክንያት ስህተት ነው" ማለት ግን ሙገታ ነው።
የሰለጠነ ሰው ሀሳብን ከሰውነት ይለያል።
* ሁለቱም ልክ ሊሆኑ ይችላሉ!
ቁጥር 6ን መሬት ላይ ጽፈን፣ እኔ ከላይ አንተ ከታች ብናየው... ለኔ 6 ነው፣ ላንተ 9 ነው። የተጣላነው እውነት ስለሌለ ሳይሆን፣ የቆምንበት ቦታ (Perspective) ስለተለያየ ነው። የሌላውን ሰው መነጽር ተውሰህ ካላየህ፣ መቼም ልትግባባ አትችልም። ማዳመጥ ማለት መስማማት ማለት አይደለም፤ መረዳት እንጂ።
ኢትዮጵያ የምትፈልገው አሸናፊ ፓርቲን ሳይሆን፣ የሰለጠነ ህዝብን ነው!
መንግስታት ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። ህዝብ ግን ዘላለም ይኖራል። በጊዜያዊ ፖለቲካ ምክንያት የዘላለም ወንድምህን አትጣላ። ፖለቲካ በምርጫ ጣቢያ ያልቃል፤ ጎረቤትነት ግን በህይወት ይቀጥላል።
💡 የቀኑ የዜግነት ፈተና (Civic Challenge):
በፖለቲካ ወይም በአመለካከት ከእርስዎ ጋር የማይስማማ፣ ምናልባትም "ከረር ያለ" ክርክር ያደረጋችሁትን አንድ ሰው አስቡ።
ዛሬ ያንን ሰው ይደውሉለት ወይም መልእክት ይላኩለት። ስለ ፖለቲካ አታውሩ። "እንዴት ነህ? ናፈቅከኝ እኮ" በሉት። ሰውየው ከፖለቲካው እንደሚበልጥ በተግባር ያሳዩ።
የውይይት መድረክ (Discussion):
ከእርስዎ ጋር ፈጽሞ በሃሳብ የማይስማማን ሰው፣ ንግግሩን ወይም ጽሁፉን ስታዩ የመናደድ ስሜትን እንዴት ነው የምትቆጣጠሩት? እስቲ "ትዕግስት"ን አስተምሩን። 👇
#ኢትዮጵያ #ፖለቲካ #መቻቻል #ሀሳብ #ነጻነት #ሰላም