
28/04/2025
የአዕምሮ ስሪትና የማረፊያ ጥበብ•••
ኢትዮጵያ|| #ጌዴኦ
አዕምሮ በሳይኮሎጂስቶች፣ በባህላዊ አባቶች፣ በግለሰቡ እንዲሁም በተለያዩ ጠቢባን፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በኪነ ጥበብ በጥልቅ ትገለጻለች።
ዊኪፒዲያ እንዲህ ይላል•••
አዕምሮ የአንድ ሰው ንቃተ ህሊና አካል ሲሆን በ"ማሰቡ"፣ በ"መረዳቱ"፣ ትዝታን በመፍጠሩ፣ ስሜትን በመረዳቱ፣ በመፍቀዱ እንዲሁም ወደፊት በመመልከቱ የሚገለጽ ነው። በአንዳንድ ፍልስፍናወች አዕምሮ ከአንጎል ይለያል። አዕምሮ እንደ አንጎል ከቁስ ነገር የተሰራ ሳይሆን በምናቡ አለም የተንሰራፋ ነው፡፡ ስለሆነም አዕምሮ ከሞላ ጎደል የማይታይና የማይጨበጥ "ሃሳብ" ስብስብ ነው።
ውስብስብ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል የሰው ልጅ ሲፈጠር በርካታ ሀሳቦች አሉት። ለመረዳት ይከብዳል። ጊዜ ሰቶ ያስባል፣ ያወጣል፣ ያወርዳል ያደላስላል ነገር ግን ከግሉ ጉዳይ ጋር ካያያዘው ውድቀቱ ከባድ ነው።
አዕምሮ የማረፊያ ስፍራውን ካወቀ፣ የተሰጠውን እንደይሁዳ ለዲያቢሎስና ለዲያቢሎሳዊያን ካላከራየ ለራሱ ቀዳሚ ተጠቃሚ ነው። ሌሊት ተነስቶ ዝናብ ሲዘንብ እያየ ተፈጥሮን ከረገመ፣ ቀኑን ለራሱ እንዲመች ካላደረገ አንድም ስኬት የለውም።
ተከፋይ አዕምሮ ሁሉም በፈጣሪ ፍቃድ ለራሱ፣ ለሰው እንዲሁም ለሌሎች እንዲሆን የተሰራ ነው። ለድሃ ማሰብ በጎነት ነው። ድሃውን ግን ማመናጨቅና መመጻደቅ ለክፋት የተከፈለው አዕምሮ ማለት ነው። አንተ እንድትሰጥ ፈጣሪ በቃሉ "ለድሃ የሰጠ ለፈጣሪው አበደረ" ብሎ ሲናገር እግዚአብሔር ይስጥህ ማለት ላይህ አልፈልግም ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለድሃው ዝም ብለህ ስታልፍ ፈጣሪ ያንተን የገዘፈ ጥያቄ የሚመልስ እንዳይመስልህ። ቃሉ እንዲህ ይላልና•••
“አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ።”
መዝሙር 49፥20
ጉንዳን 30ኛ ፎቅ ላይ ወታ ወደ መሬት ብትከሰከስ የሚሰበረው ቅስሟ እንጂ አጥንቷ አይደለም። የብዙ ሰው ሞራል ይነካ ይሆናል። ሞራል የሚነካው በሰው ልጅ አዕምሮ ነው።
አዕምሮ የተሰጠውን ኃላፊነት ካልተወጣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ትላንት ውስጥ የሚዋኝ ሰውነት፣ ለነገ ትውልድ የማያስብ፣ ባገኘው እና በተመለከተው እየተነሳ የሚያጓራ ከሆነ አዕምሮ ስራ አቁሟል ማለት ነው።
አዕምሮ ለመልካም ተሰርቷል። ክርስቶስ የይሁዳ እግሮች ያመራው፣ ያመላከተው፣ ያቀናጀው፣ ያሰለጠነው ለአገልግሎት ነበር። ነገር ግን የትንቢት መፈፀሚያ ሆኖ አምላኩ፣ የፈጠረው ጌታ እንዲሰቀል፣ ለፍርድ እንዲቀርብ አድርጎታል።
የኛ አዕምሮ ማረፊያው የት ነው? ምን ይመክራል? ለማን ይመክራል? ወዴት ያመራል? በቀን ማንን ስንት ጊዜ ይገላል? ለማን ይገዛል? ከይሁዳ ጋር ስንቴ ይውላል? ከጴጥሮስ ጋር ስንቴ ይመክራል? ከጥጦስና ዳክርስ ጋር መክሮ ከማን ጋር ውሏል?
ጥያቄው እራስን ለማየት ይረዳ ይሆናል። ለህዝብ የሚጠቅም ጥበብ እንዲገለፅ ያደርግ ይሆናል። መስከንን ያመላክት ይሆናል። እውነት መገለጫዋ የት እንደሆነ ይመሰክር፣ የናገር፣ ያስተምር ሊሆን ይችላል።
ከፈጣሪ የምትሸሽ አዕምሮ ባካኘ ናት። ከሰው የምትሸሸግ አዕምሮ ደግሞ በሻማ፣ በብርሃን፣ በጨረቃ፣ በከዋክብት ብርሃን፣ በኤሌክትሪክ ትጋለጣለች። በዚሀ መጋለጥ ውስጥ ማን ይወቀስ ይሁን? አዕምሮ፣ የአዕምሮ ባለቤት፣ የአዕምሮ ተከራይ፣ የአዕምሮ ደላላ?
ፈጣሪ በፈጠረው ለምለም መሬት ላይ ጥላቻ፣ ክፈት፣ ስድብ፣ መርገምት እና አስከፊ የትውልድ ሳንካ የተከለ እና ሌሎችም የፍርዱ መዶሻና ደወል ድምፅ ተቀባይ ሳይሆኑ አይቀሩም።
ፍርድ ግን ከአዕምሮ ፈጣሪው ነው!