
04/07/2025
እንደ ሀገር በትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን በሚደረገው ርብርብ የግብረሰናይ ድርጅት ሚና ከፍተኛ ነው ፦ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ
(ዲላ ሰኔ 27/2017 ዓ.ም ጌ ቲቪ) በሀገር ደረጃ በትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን በሚደረገው ርብርብ የግብረሰናይ ድርጅት ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ ገልጸዋል ።
ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚንስቴር እና ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተወጣጣ ልኡክ በጌዴኦ ዞን እየተተገበረ የሚገኘውን "እማጅን ዋን ደይ" ኮስታ ፋውንደሽን ታርል ፕሮግራምን ጉብኝት በማድረግ የእስካሁኑ አፈፃፀም ገምግሟል ።
"እማጅን ዋን ደይ" የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት ከኮስታ ፋውንዴሽን ታር ፕሮግራም ጋር በመሆን በጌዴኦ ዞን በሶስት ወረዳዎች ተማሪዎች የንባብና የማስላት ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው ።
በወቅቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ እንደገለጹት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ የገጠመው ችግር ስር እንዳይሰድ መንግስት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
መንግስት እያከናወነ ካለው ስራዎች ጎን ለጎን ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት ቀጣይነት ያለው ውጤት እንዲመዘገብ በተለይም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየተሰራ ስለመሆኑ አብራርተዋል ።
ለአብነትም እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብቻ 39 አጋር ድርጅቶች የትምህርት ዘርፉን በማገዝ ላይ እንደሚገኝ ወ/ሮ ፀሐይ ጠቁመው ለዚህም በክልሉ መንግስት እና በተማሪዎች ስም አመስግነዋል ።
በዘርፉ አሁን ላይ እየመጣ ያለውን መነቃቃት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ።
በትምህርት ሚንስቴር መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ሙሉቀን ንጋቱ(ዶ/ር) በበኩላቸው በዞኑ በግብረሰናይ ድርጅት እየተተገበረ የሚገኘው ተግባር ውጤታማ እንደሆነ በመግለጽ በቀጣይ ወደ ሌሎች ሀገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል ።
እንደ ሀገር መንግስት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ያሉት ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) ሁሉም የሚጠበቅበትን በመወጣት ሀገሪቷን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ።
የእማጅን ዋን ደይ (I1d) ዳይሬክተር አቶ ኡመር ሊሙ በወቅቱ እንዳነሱት ከሌሎች አጋር ድርጅት ጋር በመሆን የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል እና የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው ፕሮግራም መሆኑን አብራርተዋል ።
በፕሮግራሙ እየተተገበረ የሚገኘው ስራዎችን ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚንስትር እና ከክልል ትምህርት ቢሮ መጎበኘቱ ለቀጣይ ስራዎች የሚያበረታታ እና ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችል ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የእማጅን ዋን ደይ ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ኩሼታ ተናግረዋል ።
የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍለ በበኩላቸው በዞኑ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን እና ጠንካራ የትምህርት ስርዓትን ለመዘርጋት ስር ነቀል ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ በመግለጽ ይህም በግብረሰናይ ድርጅት እየተተገበረ የሚገኘው ስራ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል ።
@ጌዴኦ ቴሌቪዥን