18/05/2026
ከእሁዱ የአስቶን ቪላ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በኋላ፣ ማንቸስተር ሲቲ የታሪኩን ታላቅ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላን ስንብት ለማስተናገድ እየተዘጋጀ መሆኑን ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል። ለክለቡ ቅርብ የሆኑ የውስጥ አጥቂ ምንጮች እንደጠቆሙት፣ ይህ ስመ-ጥር አሰልጣኝ በዚህ የውድድር ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ ኢቲሀድ ስታዲየምን ይለቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ምንም እንኳን የማንቸስተር ሲቲ የበላይ ኃላፊዎች ጋርዲዮላ ለአንድ ተጨማሪ የውድድር ዓመት የሚቆይ ውል እንዳለው በመጥቀስ በክለቡ ይቆያል የሚል ተስፋ እንዳላቸው በይፋ ቢገልጹም፣ ከጀርባ ግን የእርሱን መልቀቅ የተመለከቱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በክለቡ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወኑ ይገኛሉ። በርካታ የክለቡ የሥራ ባልደረቦች እና የቦርድ አባላት አሰልጣኙ መውጣቱ እንደማይቀር ሙሉ በሙሉ የተረዱት ጉዳይ ሆኗል። ከተጫዋቾች ስብስብ በኩልም ከአስቶን ቪላ ጋር ከሚደረገው የዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታ በኋላ ጋርዲዮላ እንደሚሰናበታቸው እምነቱ እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ክለቡም ለዚህ ተደናቂ እና ተወዳጅ አሰልጣኝ እንዴት ያለ ታላቅ እና የሚገባውን የሽኝት ክብር ማዘጋጀት እንዳለበት ትኩረቱን ወደዚያ አድርጓል።
ዕድሜው 55 ዓመት የደረሰውን ጋርዲዮላን ለመተካት አሁን ላይ ግንባር ቀደም ሆኖ እየተጠቀሰ ያለው፣ ቀደም ሲል በማንቸስተር ሲቲ በጋርዲዮላ ሥር በረዳትነት የሠራው እና የቀድሞው የቼልሲ አሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ነው።
ፔፕ ጋርዲዮላ በኢቲሀድ ስታዲየም ባሳለፋቸው 10 የስኬት ዓመታት ውስጥ 6 የፕሪሚየር ሊግ፣ 1 የሻምፒዮንስ ሊግ፣ 3 የኤፍኤ ካፕ እና 5 የሊግ ካፕ ዋንጫዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 20 ታላላቅ ዋንጫዎችን ለክለቡ ማምጣት ችሏል። በታሪክ ፈጽሞ ወደማይገኝበት የከፍታ ማማ ላይ ሲቲን ያወጣው እና በብዙዎች ዘንድ የዓለማችን የምንግዜም ምርጡ አሰልጣኝ ተደርጎ የሚወሰደው ጋርዲዮላ፤ በዚህ የውድድር ዓመት አስቀድሞ የኤፍኤ ካፕ እና የካራባኦ ካፕ ዋንጫዎችን ያነሳ ሲሆን፣ እሁድ ዕለት ደግሞ 7ኛውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ በማንሳት ወርቃማውን የማንችስተር ሲቲ ዘመኑን በደማቅ ሁኔታ ሊያጠናቅቅ ከደጃፍ ደርሷል።