09/10/2025
የሀገሪቱ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ የነደፈዉን ፖሊሲ ቀድመዉ በመተግበር ዉጤታማ የሆኑ የዱራሜ ከተማ አርሶ አደር አቶ ስምኦን ያዕቅም፦
ነዋሪነታቸው በዱራሜ ከተማ በላሎ ከተማ ቀበሌ ዌታ መንደር ነዉ አርሶ አደር ስምኦን ያዕቅም።
ጅማሮያቸዉን ምንም እንኳን ትምህርታቸዉን በአግባቡ በመከተል በመንግሥት ሥራ ላይ ቢሰማሩም ከወር እስከ ወር ተጠብቆ የሚገኘዉ ደሞዝ እሳቸው በሚፈልጉት ልክ በሳቸውና በቤተሰባቸው ሕይወት ላይ ተጨባጭ ውጤት ሊያመጠላቸው ባለመቻሉ እና ለዚህም በግብርናው ዘርፍ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው እራሳቸውን በማሳመን ቆርጠዉ በመነሳት የግብርና ሥራ መጀመራቸውን ይናገራሉ።
አርሶ አደሩ የሀገሪቱ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ የነደፈውን የግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀድመው በመተግበር በርካታ አመርቂ ዉጤቶችን ማስመዝገባቸው ደግሞ ህያዉ ምስክር ሆኖ በመሬት ላይ ደምቆ፣ ጎልቶ፣ እና በውጤት አሸብርቆ እንዲታይ አድርገዋል።
በዚህም የብልጽግና መንግስት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የግብርና ፖሊሲዎችን ነድፎ ያስቀምጥ እንጂ እኚህ ምሁር፣ ታታሪና ሞዴል አርስ አደር በአካባቢያቸው ያለውን የመሬት፣ የሰውና መሰል የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶችን/ፀጋዎችን በአግባቡ በመጠቀም በቁርጠኝነት ተግባራዊ አድርገዉ የተገኙ መሆናቸውን በቃላቸውና በሠናይ ምግባራቸው ጭምር አብራርተዋል።
የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ ጥምር ግብርና ላይ ትኩረታቸውን በማድረግም ዉጤታማ የግብርና ሥራ አከናዉነዋል ሞዴል አርሶ አደር ስምኦን ያዕቅም።
በአካባቢው ያለውን ሀብት በመለየት ፣ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀምና እና ልዩ ትኩረት በመስጠት ከተሰራ ዉጤታማ መሆን የሚከለክል አንዳች ስንኳን እንደሌላ የሚናገሩት አርሶ አደሩ በዚሁ መነሻ ዉጤታማ የግብርና መንገድ በመከተል ከራሳቸዉ አልፈዉ ለሌሎችም ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደፈጠሩ ይናገራሉ።
ጅምር ላይ አንድ የወተት ላም እንደነበራቸዉ የሚነግሩት ሞዴል አርሶ አደር አቶ ስምኦን ከስኬታማ ወንድ ጀርባ ሁሌም ጠንካራና ታታሪ ሴት አለች እንደሚባለው, ከፀባይ ሠናይ ጠንካራ ሥራ ወዳድና ሰው አክባሪ ከሆኑ ከባለቤታቸው ከገነት ዮናስ ጋር በጋራ በመሆን እየሠሩ ባሉት ጠንካራ ሥራ በአሁን ሰዓት ከ10 በላይ ዘመናዊ የወተት ላሞችን በማድለብ ከእርሻ ሥራቸው ባሻገር ወተት እና የወተት ተዋፅኦ የገቢ ምንጫቸው እንደሆነ በመናገር ልጆቻቸውን በአግባቡ በማስተማር ለቁምነገር እንዲበቁ በማድረግ ሥራ ወዳድ፣ ውጤታማና ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ የወላጅነት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ይገኛሉ።
የመንግሥት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመከተል የተለያዩ ለማሳ ለሚነት ጠንቅ የሆኑ እንደ ባህር ዛፍ ያሉ የማይበሉ ዛፎችን በመንቀል የተጎዱ ማሳዎቻቸውን በማከም፣ ወደ እህል፣ ፍራፍሬ ፣ የቡናና መሰል ጠቃሚ ወደ ሆኑ ምርቶች በመቀየር በተላይ መንግስት ያስጀመረውን የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ በማሳካት ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ለአካባቢው ፣ ለከተማውና ለሌሎችም አካባቢ አርሶ አደሮች አርአያ የሆኑ ውጤታማ አርሶ አደር መሆናቸውን ከከተማ፣ ከዞን፣ ከክልል፣ ብሎም እስከ ፌድራል ያሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ማሳቸውንና መኖሪያ ቤታቸውን በመጎብኘት ምስክርነታቸውን ሰጥቷቸዋል።
አቶ ስምዖን ያዕቅም የዉበት ፣የምግም፣ ኢንቨስትመንት እና አረንጓዴ አከባቢ የመፍጠር ሥራ የመሥራት ተግባራቸውን በማጠናከር ጠንካራ የግብርና ግስጋሴያቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውም ተመልክቷል።
በትንሽ ቦታ በርካታ የግብርና ተግባራትን በማከናወን እና ጥምር ግብርናን እውን በማድረግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሆነም ጭምር አብራርተዋል ሞዴል አርሶ አደሩ።
ታዲያ በትንሽዬ መኖርያ ቤት ገና አሃዱ በማለት ህይዎታቸዉን የጠነሰሱት ምሁሩ፣ ሥራ ወዳዱ፣ ጠንካራና ሞዴል አርሶ አደር ስምዖን ያዕቅም ሥራ ሳይንቁ ጠንክሮ በመሥራት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ትርጉም ባለው መልኩ ቀይረዋል፣
ከራሳቸው አልፈው ለበርካታ አካባቢው ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር የቻሉ ትጉህ ሞዴል አርሶ አደር ናቸው።
በአሁን ጊዜ እጅግ ዘመናዊና ቅንጡ መኖሪያ ቤት ባለቤት ከመሆናቸውም ባሻገር መንግስት በከተማ የተጀመረው የዜጎችን ሕይወት በመልካም በመቀየር ይህንኑ መልካም እሳቤ ወደ ገጠሩ ማህበረሰብ በማስፋፋት የጀመረው የገጠር ኮርደር ልማት አስቀድመው አሳክተዋል።
አቶ ስምዖን ያዕቅም ለሌሎችም አርኣያ የሚሆኑ ጠንካራ ሞዴል አርሶ አደር መሆናቸውን በተግባር ያረጋገጡ የልማት አርበኛ መሆናቸውን እኛም በቤታቸውና በማሳቸው ተገኝተን ምልከታ በማድረጋችን የዓይን ምስክሮች ነንና እንደ ሞዴል አርሶ አደር ስምዖን ያሉ ጠንካራና ውጤታማ አርሶ አደሮች እንዲበዙ ምኞታችን ነው።