
29/07/2025
«ሐጅ ሙሐመድ ሳኒን ማን ይተካቸው? » ትግልና ምርጫው
🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴
በአሕመዲን ጀበል
🚘🚘🚘🚘🚘
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችን ያቋቋሙና የመሩ አባቶች ምን ያክል ሩቅ አሳቢና ስትራቴጂያዊ ተላሚ፣ የተቋሙንም ሆነ የሕዝበ ሙስሊሙን ጥቅም አሳልፈው ላለመስጠት ይጠነቀቁ እንደነበሩ የሚጠቁሙ በርካታ የታሪክ አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል። በዚህ ጽሑፍ ከእነዚህ ክስተቶች መካከል አንዱ የሆነውን አንመለከታለን።
ይኸውም የመጅሊስ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ በሞት ሲለዩ፣ በእርሳቸው ቦታ ምትክ ለመምረጥ ለተተኪው ተመራጭ እጩ ምን ዓይነት መስፈርት እንዳስቀመጡና ተገቢውን ሰው ለመምረጥ ምን ያክል ጥንቃቄ እንዳደረጉ የምናይበት ነው። ታሪካዊ ክስተቱም ለኛ ትውልድም ብዙ የሚያስተምረው ነገር አለ።እንዲህ ነበር።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መጋቢት 4 ቀን 1968 በይፋ ከተመሰረተ አንስቶ በተወዳጅነትና በሕዝብ ይሁንታ ለ12 ዓመታት መጅሊስን በፕሬዝዳንትነት መርተዋል። ሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ የመጅሊስ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት፣ በኢስላማዊም ሆነ በአካዳሚክ ትምህርት ራሳቸውን ብቁ አድርገው የተገኙ ነበሩ። በአካዳሚክ በኩል ኪታብ ከቀሩና እድሜያቸው ከገፋ በኋላ ነበር ለሌሎች መሻይኮች አርኣያ በሚሆን መልኩ መደበኛ ትምህርት ተምረው የሁለተኛ ደረጃን ያጠናቀቁት።ከመማርም አልፈው በአካዳሚክ መምህርነት ተመድበው በአስመራ፥ በደሴ ወይዘሮ ስህንና በአዲስ አበባ በደጃዝማች ዑመር ሰመተር ትምህርት ቤቶች በመምህርነት አገልግለዋል።
በኢስላማዊ አስተዋጽኦ በኩል ከአንዋር መስጂድ ኢማምነት ባሻገር ቁርኣንን ከሼይኽ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ ጋር ለመጀመሪያ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉመዋል። የተለያዩ ኢስላማዊ መጽሐፍትን በአማርኛ ቋንቋ ጽፈዋል።
ሐጂ ሙሐመድ ሳኒ በማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍም የሙስሊም ወጣቶችን በማደራጀትና በማሰልጠን ፣ ከዚያም አልፈው በታሪካዊው የሙስሊሞች የ1966 ሰልፍ ከጥንስሱ ጀምሮ ሰልፉን በማደራጀትና ከፊት በመምራት የመሪነት ሚናቸውን ተወጥተዋል።
በመጅሊስ ፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ለሕዝበ ሙስሊም ጥቅምና ጉዳይ ከመጠመድ ዉጭ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው የተለየ ክብርና ጥቅም ለማግኘት ሳይመኙ ከቆሙለት ዓላማ ዉጭ ግራ ቀኝ ሳያዩ ለሕዝበ ሙስሊሙ ተግተዋል። በመሪነታቸው ዘመንም ሆነ ካለፉ በኋላ በክፉ ሳይነሱ ስማቸውንና ክብራቸውን ጠብቀው ለመገኘት በእጅጉ ይተጉ ነበሩ።
የሕዝበ ሙስሊሙ ሆነው በርካታ ፈተናዎችን አሳልፈዋል። እርሳቸው የመጅሊስ ፕሬዝዳንት እያሉ ነበር የደርግ መንግስት ሁለት ልጆቻቸውን በቀይ ሽብር የረሸነባቸው። በርሳቸውም ላይ ብዙ ፈተና ደርሶባቸዋል። ሆኖም የሙስሊሙ ተወካይነታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ በራሳቸውና በልጆቻቸው ላይ የደረሰባቸውን ሁሉ ችለው ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው ጥቅም ሲሉ በትዕግስት ሚናቸውን ተወጥተዋል። በስልጣን ዘመናቸው በሁሉም የሙስሊም ህብረተሰብ ዘንድ ተወዳጅና ቅቡል እንደሆኑ የመሪነት ሚናቸውን ተመጡ።
ሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ በሚያዚያ 20 ቀን 1981 ወደ ማይቀረው ቀጣይ ዓለም ተሻገሩ (አላህ ይዘንላቸዉ) ። ሕዝበ ሙስሊሙ ከጫፍ እስከ ጫፍ በሚወዳቸው መሪው ሞት የሐዘን ድባብ ዋጠው። ሕዝበ ሙስሊሙና ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን በእንባ እየተራጩ አስክሬናቸውን ከፍ ባለ አጀብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ አስቀበራቸው።
ቀጣዩ የሕዝቡ ጥያቄ «ሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብን ማን ይተካቸዋል?» የሚል ሆነ። ቀጥሎም እርሳቸውን የሚተካን መሪ ለመምረጥ ምርጫ ለማካሄድ ታሰበ። በዚህ ጊዜ ሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ተቀምጠው በመሩበት ወንብር የተለያዩ ወገኖች የየራሳቸውን ሰዎች መሪ አድርገው ለማስቀመጥ እንቅስቃሴ ጀመሩ። የደርግ መንግስትም ለእርሱ የሚመች የራሱን ሰው በመጅሊስ ፕሬዝዳንትነት ላይ ለማስቀመጥ መንቀሳቀስ ጀመረ።
መንግስትም ሆነ የየራሳቸውን ሰው በመጅሊስ ፕሬዝዳንትነት ለማስቀመጥ የሚንቀሳቀሱ አካላት ይህንኑ ዓላማቸውን ለማሳካትም የተለያዩ ስልቶችን ቀይሰው መንቀሳቀስ ጀመሩ።
በመጅሊስ የሥራ አስፈጻሚዎችና ወሳኝ የሚባሉ አካላትን ሞራል ለመንካት፣ በመካከላቸው ክፍፍል ለመፍጠርና ቅራኔ ለመፍጠር፣ የተሳሳቱ ዉሳኔዎችን እንዲያሳልፉ ለማድረግ ጫና ለመፍጠር በእነርሱ ላይ የሥም ማጥፋት ዘመቻ ማድረግን ተያያዙት። ይህን ማሳካት ካቃታቸው መጅሊስ ራሱ እንዳይኖር በሚልም ጥረታቸውን ገፉበት። ከሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ጋር የሥራ አስፈጻሚ የነበሩት የመጅሊስ አባላት ደግሞ በበኩላቸው ይህንኑ የተሸረበውን ሴራ ለማክሸፍ ጥረታቸውን ሌላ አቅጣጫ ቀጠሉ።
ስለዚሁ የመጅሊስ ፕሬዝዳንት ምርጫና የራስን ሰው በፕሬዝዳንትነት የማስቀመጥ ትንቅንቅን «ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና የመጅሊስ ፈተና» የተሰኘው የአቶ ሰዒድ ሙሐመድ አወል መጽሐፍ ገጽ 313 ላይ ከወቅቱ የጉባዔው አባል ከነበሩትና በቅርቡ ወደ አኺራ ከሄዱት ሐጂ ደርባቸው ሙሐመድ (አላህ ይዘንላቸዉ) ጋር ሑኔታውን አስመልክቶ በቃለ-መጠይቅ ያገኘውን መረጃ ቃል-በቃል እንዲህ አስፍሮታል: -
«ከሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ሞት በኋላ ተተኪዉን ለመመረጥ በሚታስብበት ጊዜ ስለምርጫዉ አፈጻጸም በአወጣነዉ የምርጫ ደንብ ዉስጥ የሚመረጠዉ ሰዉ የኸለዋ ሰዉ ሳይሆን፣ የሚደርስበትን ችግር ተቋቁሞ ሊመራ የሚችል፣ ዑለማ የሆነ፣ አረብኛ የሚችል ደፋር …. የሆነ የሚል መስፈርት ስለነበር በዚሁ መሰረት በምርጫዉ ጊዜ ለቦታዉ ይመጥናሉ የተባሉ ሰዎች ሲጠቆሙ የሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ሸሪካ የሆኑት ታላቁ ዓሊም ሸኽ ሙሐመድ ታጁ (አላህ ይዘንላቸዉና) ይሁኑ ተብለዉ ተጠቁመዉ የነበረ ሲሆን፣ ግለሰቡ ታላቅ ዓሊምና ለቦታዉ የሚመጥኑ መሆናቸዉ ምንም ጥርጥር የሌለው ቢሆንም፣ ነገር ግን በጉባዔዉ አመራር ላይ ከመንግሥት ባለሥልጣን አልፎ ሙስሊም ነን በሚሉ ጠላቶች በየጊዜዉ እየተቦረቦረ እንዲፈርስ ከፍተኛ ችግር የሚያደርሱ ሰዎችን ተንኮል ተቋቁመዉ ለመስራት ሊቸገሩ ስለሚችሉ እሳቸዉ ቀርተዉ በጎንደር የተወለዱትና በግብጽ የተማሩት ዑለማ፣ አንደበተ ርቱዕ፣ ደፋር፣ አረብኛ፣ አማርኛና ትግረኛ ቋንቋ የሚናገሩትን፣ የዉጭም የዉስጥም ችግር ቢደርስባቸዉ ተቋቁመዉ ሊመሩን ይችላሉ ያልናቸዉን የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ሐጂ ዑመር ሑሴን አብዱልዋሂድን በሊቀመንበርነት መረጥን፡፡» ።
በዚህ የሐጂ ደርባቸው ገለጻ ዉስጥ በርካታ ቁም ነገሮች ተጠቅሰዋል። የዚያን ጊዜ የምርጫው ያልጻተፍ ማኑዋል ለመጅሊስ ፕሬዝዳንትነት የሚመረጥ ሰው ምን ዓይነት መስፈር ማሟላት እንዳለበት ከታች የተገለጹት መስፈርቶች ናቸው። እነርሱም፦
1. «የኸለዋ ሰዉ ሳይሆን» ፥ከሕዝቡ ራሱን ነጥሎ ለአምልኮ ዓላማ በመስጊድ የሚቆይ ያልሆነ ሰው።
2. «የሚደርስበትን ችግር ተቋቁሞ ሊመራ የሚችል»፣
3. ዑለማ የሆነ፥
4. አረብኛ የሚችል፥
5. ደፋር የሆነ። የሚሉ ነበሩ።
የተጠቆሙት እጩ ለምን ሳይመረጡ ቀሩ?
🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴
በተቀመጡት መስፈርቶች መሠረት ሸኽ ሙሐመድ ታጁ በእጩነት ተጠቆሙ። ሆኖም መራጩ ጉባኤ እርሳቸውን ሳይመርጥ ቀረ። ምክንያቱንም ሐጂ ደርባቸው እንዲህ ሲሉ ያስቀምጡታል: -
«ግለሰቡ ታላቅ ዓሊም፣ ለቦታዉ የሚመጥኑ መሆናቸዉ ምንም ጥርጥር የሌለው ቢሆንም፣ ነገር ግን በጉባዔዉ አመራር ላይ ከመንግሥት ባለሥልጣን አልፎ ሙስሊም ነን በሚሉ ጠላቶች በየጊዜዉ እየተቦረቦረ እንዲፈርስ ከፍተኛ ችግር የሚያደርሱ ሰዎችን ተንኮል ተቋቁመዉ ለመስራት ሊቸገሩ ስለሚችሉ እሳቸዉ ቀርተዉ» (ገጽ 313)
በዚህ ገለጻ መሠረት እጩ ፕሬዝዳንቱ ለመመረጥ የዒልም ብቃት መመዘኛውን ቢያልፉም ለፕሬዝዳንትነት እንደማይሆኑ የታመነው በሚከተሉት ምክንያቶች ነበር።
1) ከመንግስትና ከዉስጥ አፍራሾች የሚመጣውን ጫና መቋቋም እንደማይችሉ በመታመኑ።
2) መጅሊስን ለማፍረስና ለማዳከም ከዉስጥ እየቦረቦሩ ያሉ አካላትን ተንኮል መቋቋም እንደማይችሉ በመታመኑ።
ተመራጩ በምን መስፈርት ተመረጡ?
የመጅሊስ ፕሬዝዳንትን ለመምረጥ ተሰየመው ጉባኤ የሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብን የቅርብ ወዳጅና ሸሪክ የነበሩትን ሐጅ ሙሐመድ ታጁን መምረጥ ትቶ፣ የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ሐጂ ዑመር ሑሴን ዓብዱልዋሂድን በሊቀመንበርነት መረጠ። ይህን ለማድረጉ የተጠቀሰው ምክንያት ደግሞ እንዲህ በሚል በታሪኩ ዉስጥ ሰፍሯል፦
«በጎንደር የተወለዱትና በግብጽ የተማሩ ዑለማ፣ አንደበተ ርቱዕ፣ ደፋር፣ አረብኛ፣ አማርኛና ትግረኛ ቋንቋ የሚናገሩትን የዉጭም የዉስጥም ችግር ቢደርስባቸዉ ተቋቁመዉ ሊመሩን ይችላሉ ያልናቸዉን የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ሐጂ ዑመር ሑሴን ዓብዱልዋሂድን በሊቀመንበርነት መረጥን፡፡» (ሰዒድ ሙሐመድ አወል፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና የመጅሊስ ፈተና፣ ገጽ 313)
የተመራጩ ፕሬዝዳንት ለለመረጣቸው እንደብቃት የታዩላቸው የሚከተሉት ነጥቦች ነበሩ፦
1) በዉጭና ሀገር ውስጥ የተማሩና የዉጩውን ዓለም ሁኔታ ማየታቸው፣
2) አንደበተ ርቱዕ መሆናቸው፣
3) ደፋር መሆናቸው፥
4) የተለያዩ ቋንቋዎችን መቻላቸው፣
5) የዉጭና የዉስጥ ጫናን ተቋቁመው ሊመሩ እንደሚችሉ መታመኑ፣
6) የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተቋሙን የመምራት የሥራ ልምድ ያላቸው መሆኑ።
መጅሊስን ማዳከም የሚፈልጉት አካላት መስፈርቶች
💢💢💢💢💢💢💢💢💢💢💢💢💢💢💢
መንግሥትና መጅሊስ እንዲዳከም ይፈልጉ የነበሩ አካላትና የየራሳቸውን ሰዎች በመጅሊስ ፕሬዝዳንትነት ለማስመረጥ ይፈልጉ የነበሩት አካላት ሁሉ፣ በሐጂ ዑመር ሑሴን ዓብዱልዋሂድ መመረጥ ደስተኞች አልሆኑም። እናም ሁኔታው ወደሌላ አቅጣጫ መሄድ ጀመረ።
«የጉባዔዉን መጠናከር የማይፈልጉትና እንዲፈርስ ካልሆነም እነሱ የሚፈልጉት ጉባዔዉን ሽባ የሚያደርግ ሰዉ እንዲመረጥ የሚፈልጉት ወገኖች፣ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሱዳናዊ፣ ናይጀርያዊ ተመረጠ የሚል አሉባልታ ከማናፈስ አልፈዉ ለባለሥልጣን አቤቱታ አቀረቡ፤ ይህንኑ መነሻ በማድረግም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አንድ መሆንና መጠናከር የማይፈልጉት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሃይማኖት ጉዳዮች አስተባባሪ ሚኒስትሩ ምርጫዉ ትክክል አይደለም ፤ ምርጫዉን ሰርዣለሁ፣ ለዚህ ሁሉ ምክንያቶቹ ሁለቱ ምክትል ሊቃነ መናብርትና ዋና ጸሐፊዉ በመሆናቸዉ ስራ እንዳይሰሩ በማገድ ሌሎች ተመራጮች ይመሩታል በማለት አስደንጋጭ የቃል ዉሳኔ አስተላለፉ፡፡»
(ሰዒድ ሙሐመድ አወል፥ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና የመጅሊስ ፈተና ፥ ገጽ 313)
በሐጂ ዑመር ሑሴን ዓብዱልዋሂድ መመረጥ ያልተደሰቱ አካላት ምክንያትና ሁኔታን በግልጽ እንድንረዳ የሚያደርጉልን ነጥቦች ከዚህ አጭር ገለጻ በሚገባ ተጠቅሷል። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፦
1) መጅሊስን ሽባ የሚያደርግ ሰው እንዲመረጥ ይፈልጉ ነበር፣
2) የማይፈልጉት ሰው ሲመረጥ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ነዙ። የዉጭ ዜጋ ተመረጠ ብለው ከሰሱ፣
3) የሚፈልጉት ሰው ስላልተመረጠ ጉዳዩን ወደ መንግሥት ወሰዱት፣
4) አጀንዳውን ይዘው የሄዱት ደግሞ ቀድሞውኑ የሙስሊሞችን አንድነት ወደማይፈልግ የመንግሥት ባለሥልጣን ነበር፣
5) እነርሱ የሚፈልጉት ሰው ስላልተመረጠ ብቻ «ምርጫው ትክክል አልነበረም» የሚል ዉንጀላ በመሰንዘር አቤቶታ አቀረቡ፣
6) መንግሥትም እንዲመረጥለት የሚፈልገው ሰው ስላልተመረጠ ብቻ «ምርጫውን ሰርዣለሁ» አለ።
7) መንግስት እኔ የምፈልገው ሰው በመጅሊስ መሪነት እንዳይመረጥ ያደረጉት ሁለቱ ምክትል ሊቀመናብርትና ዋና ጸሐፊ ሆነው የተመረጡት ናቸው በሚል፣ የእነርሱን ምርጫ ጭምር አገደ። ከዚያም ሌሎች ተመራጮች ይመሩታል የሚል ዉሳኔ አሳለፈ፣
😎 በአብላጫ የሕዝብ ድምጽ የተመረጡትን የፕሬዝዳንቱን ምርጫንም ጭምር መንግሥት ሰረዝኩኝ አለ፣
9) ለመጅሊስ የሚያስፈልግና ለሕዝበ ሙስሊሙ የሚጠቅም መንግሥት ግን የማይፈልጋቸው ሰዎች በመመረጣቸው ሚነስትሩ ጥላቻውን ገለጸ፣
10) መንግሥት የመጅሊስ መሪነትን እንዲይዙለት ያዘጋጃቸውን ሰዎች ዳግም ለማስመረጥ ሚስጥራዊ እንቅስቃሴ ጀመረ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ «ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና የመጅሊስ ፈተና» የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ተጨማሪ ገለጻ አስፍሯል፦
«ሚኒስትሩ ሐጂ ዑመር ሑሴን ዓብዱልዋሂድ በሊቀመንበርነት መመረጥ ሕጋዊ አይደለም በማለት ምርጫውን ውድቅ ከማድረጋቸው አልፈው ተርፈው ለዚህ ምክንያት ሁለቱ ምክትል ሊቀመናብርትና ዋና ጸሀፊዉ ናቸው በማለት በሕዝብ ሙስሊሙ የብዙኀን ድምፅ የተመረጡትን ከስራ ይታገዱ በማለት የቃል ትዕዛዝ በመስጠት ጥላቻቸውን በገሃድ በማሳየት በተጨማሪም ሌሎች ጉባኤውን የሚመሩ ሰዎች ይመረጣሉ በማለት በምስጠር ያዘጋጇቸውን ግለሰቦች አመራሩን በቅርቡ እንደሚይዙ በመደንፋት የአመራር አካላቱን ከቢሮቸው አባረሯቸዉ፡፡» (ገጽ 313)
ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን? እስቲ ምከሩበት።ለዛሬ በዚሁ አበቃሁ።ይቀጥላል፦