20/05/2026
በሀገር አቀፍ ደረጃ የፋይዳ መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር 43 ሚሊየን ደረሰ
++++++++++++++
| በኢትዮጵያ የብሔራዊ መታወቂያ ፋይዳ ተመዝጋቢዎች ቁጥር 43 ሚሊየን መድረሱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ዲጂታል መታወቂያን ከ100 በላይ በሚሆኑ የመንግሥትና የግል ተቋማት አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር ዜጎች መረጃን መሰረት ያደረጉ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አስችሏል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመላከቱት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 20 ሚሊየን ዜጎች ለብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝግበዋል፡፡
ይህም በመላው ሀገሪቱ የብሔራዊ መታወቂያ ፋይዳ ተመዝጋቢዎችን ቁጥር 43 ሚሊየን እንዳደረሰው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በዲጂታል ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆነውን የሞባይልና የኢንተርኔት ተጠቀሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ በተሰራው ሥራ በሀገሪቱ በአጠቃላይ 97 ሚሊዮን ዜጎች የሞባይል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 84 ሚሊዮኑ በኢትዮ ቴሌኮም፣ 13 ሚሊዮኑ ደግሞ በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኩል የተመዘገቡ ናቸው ብለዋል፡፡
የኢንተርኔት ተደራሽነት ለማሳደግ በተሰራው ሥራ በኢትዮ ቴሌኮም 49 ነጥብ 9 ሚሊዮን፣ በሰፋሪኮም ኢትዮጵያ 11 ነጥብ 1 ሚሊየን በድምሩ 61 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠንና ዜጎች አስተማማኝ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በክብረአብ በላቸው
#ጋዜጣፕላስ #ኢትዮጵያ #ፋይዳ #ዲጂታል #ኢትዮጵያ #ኢንተርኔትተጠቃሚዎች