01/09/2025
"የኢትዮጵያ ማንሠራራት ጅማሮ"
የኢትዮጵያ ታሪክ በብዙ ውጣ ውረዶች፣ ትግሎች እና ጀግንነቶች የተሞላ ነው። በየዘመናቱ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበርና ነፃነትን ለማስረገጥ አባቶቻችን እና እናቶቻችን የከፈሉት መስዋዕትነት ደማቅ ነው።
አሁን ደግሞ ሀገራችን አዲስ የመንሰራራት ዘመን ጅምሬ ላይ ትገኛለች። የዚህ ዘመን ምልክት ደግሞ የሕዳሴው ግድብ ነው።
ይህ ግድብ የብረት እና ኮንክሪት ስብስብ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያን የመነሳትና ራስን የመቻል መንፈስ ህያው ምስክር ነው። የኢትዮጵያ ማንሠራራት ጅማሮ የብዙ ትናንሽ ጠብታዎች ድምር ውጤት መገለጫ ነው።
የህዳሴ ግድባችን በ'ደም ጠብታ!' የሚገለጽ ነው። ይህም የሀገራችን ህልውና እና የሉአላዊነት ዋጋን ያመላክታል። የጠላት ጥቃት በተደቀነ ጊዜ የሀገርን ክብር ለማስጠበቅ የወደቁ ጀግኖች ደም ይገልጻል። ለሀገራቸው የከፈሉት የመጨረሻ ዋጋ ይመሰክራል። ይህ ደም ለሀገራችን ህይወት የሰጠ ነው። ለውጭ ጠላቶች ሳይበገር ኢትዮጵያዊነትን አጽንቶ የኖረ ነው። በተመሳሳይም የህዳሴ ግድብ ግንባታ ብዙ ውጣ ውረዶች እና ብርቱ ትግሎችን በጽናት መሻገር የጠየቀ ነው። የተለያዩ ሴራዎችን እና ችግሮችን በጽናት በመቋቋም የተገኘ የላቀ እና የደመቀ ታሪካዊ ስኬት ነው። ዛሬ ግድባችን የተሻገርነው የደም መስዋዕትነት እና የትግል ምልክት ሆኖ በታላቅ ድምቀት ለምረቃ ሊበቃ ከፊታችን ቆሟል።
የህዳሴ ግድባችን 'የላብ ጠብታ!' ነው። ይህ የኢትዮጵያውያን የድካም ፍሬ፣ የጥረታቸው እና የቁርጠኝነታቸው ምስክር ነው። ግድቡን የዛሬው ቁመናው ላይ ለማድረስ ያወጡት ገንዘብ፣ የገበሩት እውቀት እና ያፈሰሱት ላብ መገለጫ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቀን ከሌሊት በትጋት ያንጠባጠቡት ላብ የሚያሳይ ድንቅ አሻራ ነው።
ህዳሴ ግድባችን የኢትዮጵያውያን የሀዘን፣ የተስፋ እና የትግል ዕንባ ነው። ይህ የብዙ ዘመናት የድህነት፣ የሀዘን የቁጭት እና የብስጭት ዕንባ ዛሬ የህዳሴ ግድብን እውን አድርጓል። ይህ ግድብ ለትውልድ የሚታይ ተስፋን እና ደስታን የሚያበስር፣ የዕንባ ጠብታን ወደ ደስታ ዕንባ የቀየረ ነው። ህዳሴ ግድብን የኢትዮጵያ ማንሠራራት ጅማሮ ከሚያደርጉት ቁልፍ ነጥቦች አንዱ ነው።
የህዳሴ ግድብ 'የውሃ ጠብታ’ ነው ። በእርግጥም የውኃ ጠብታ የህይወት እና የብልጽግና ምንጭ ነው። ይህ ግድብ የሀገራችን እድገት፣ ለትውልድ ህይወት እና ብልጽግና ምንጭ መሆኑን ያሳያል። ይህ ግድብ የሀገራችን የኢኮኖሚ ህይወትና የእድገት ምንጭ እንደሆነ ያረጋግጣል። የዚህ ዘመን ትውልድ እና አመራር በራስ መተማመን እና ቁርጠኝነት የአገራችን ማንሰራራት ጅማሬን ያበስራል።
በአጠቃላይ ይህ ግድብ በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት፣ መስዋዕትነት እና እምነት የተገኘ ነው። ጠቅላይ ሚንስትራችን እንደጠቀሱት “የደም ጠብታ፣ የላብ ጠብታ፣ የዕንባ ጠብታ፣ የውኃ ጠብታ" ድምር ውጤት ነው። ይህ ግድብ ህያው ምልክት ሆኖ 'ለትውልድ ሲመሰክር የሚኖር ቋሚ ምስክር ነው'።