
24/05/2024
የወሊድ መቆጣጠሪያ መውሰድ ይቻላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወሊድ መቆጣጠሪያ ምን ይላል?
ከሰዎች ወቅታዊ ችግር አንጻር እንዴት ይታያል?
በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
ሼር በማድረግ ላላወቁ አሳውቁ
ተወዳጆች ሆይ በዚህ ርእስ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት ሥርዐት እና ከሰዎች ወቅታዊ ችግር አንጻር በሰፊው እንመለከታለን፡፡
የወሊድ መቆጣጠርያ መውሰድ ይቻላል ወይስ አይቻልም ብለን ስናስብ በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር መለኮታዊ እቅድ እና ሐሳብ ብሎም የሰውን ልጅ ዘር ከማስቀጠል ጋር ነው የምንጋጨው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር መውለድን ተቆጣጠሩ ሳይሆን በመውለድ ተባዝታችሁ ኑሩ ነው ያለን፡፡ እኛ ገና ያልተፈጠሩት ልጆች በወሊድ መቆጣጠሪያ ወደዚህች ምድር እንዳይመጡና ከእኛ አብራክ እንዳይወለዱ እንከላከላለን፡፡ ግን ልዑል እግዚአብሔር ገና ሳንፈጠር አካላችን በእናታችን ማሕፀን ሳይሠራ፣ ነፍሳችን በሥጋችን ሳትዘራ ያውቀናል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ አካሌን ቀኖቼ ሁሉ አንድስ እንኳ ሳይኖር በመጽሐፍ ተጻፉ›› ያለው፡፡
ወዳጆቼ እግዚአብሔር በማሕፀን ሳንሠራ አካላችንን ያውቃል ያያል፡፡ /መዝ 139፣16/ እንዲሁም እግዚአብሔር እኛ ገና ለገና ሳይፈጠሩ የወሊድ መቆጣጠሪያ ወስደን እንዳይወለዱ የምንከላከላቸውን ልጆች አስቀድሞ ሳይፈጠሩ እንደሚያውቃቸው በመጽሐፈ ኤርሚያስ ላይ ‹‹በሆድህ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ›› በማለት ተናግሯል፡፡ ስለዚህ እኛ መውለድ እየቻልን ግን በወሊድ መቆጣጠሪያ ይምከኑ አይምከኑ የማናውቃቸው ልጆች በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት›› ብሎ በቡራኬ አዞናል፡፡ ግን እጅጉን በሚያሳዝን ሁኔታ ዛሬ ልጆች እንደ ሸክም ተቆጥረዋል፡፡ እኛ አንወልድም እያልን በወሊድ መቆጣጠሪያ የምንከላከላቸው ልጆች መካኖች መውለድ የሚመኟቸው ልጆች ናቸው፡፡ እኛ ለምለም ማሕፀን ይዘን ልጅ መውለድ አልፈልግም የምንለው መካኖች ዐሥር በወለድኩበት የሚሉበት ማሕፀን ነው፡፡
እግዚአብሔር በመጀመሪያ ደረጃ የወሊድ መቆጣጠሪያን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተቃወመው በይሁዳ ልጅ በአውናን ነው፡፡ ትዕማርን ያገባው ዔር ክፉ ስለነበር አካሄዱም ከእግዚአብሔር መንገድ የወጣ ስለሆነ እግዚአብሔር ቀሠፈው ሞተ፡፡ ምስኪኗ ትዕማርም ያለ ባል ቀረች፡፡ ከዚያም ለሟቹ ለዔር ወንድም ለአውናን በጋብቻ ተሰጠች፡፡ አውናንም እንደ ወንድሙ ክፉ ነበርና ያለውን ርስት ገና ለገና በሟች ወንድሙ ፈንታ ለሚወልዳቸው ልጆች ላለማካፈል ብሎ በወቅቱ በነበረው የእርግዝና መከላከያ ዘዴ እና በነበረው ልምምድ ከትዕማር ጋር ሩካቤ ሥጋ ሲፈጽም ዘሩን ከማሕፀንዋ ውጭ እያፈሰሰ እርግዝናን ይከላከል ነበር፡፡ ይህንን ተግባሩን መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት፣ እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው›› ይለናል፡፡ /ዘፍ 38፣10/ ወዳጆቼ አውናን በወቅቱ በነበረው ልምድ ባደረገው እርግዝና መከላከያ ዘዴ እርሱም ዘርን ከማሕፀን ውጪ በማፍሰስ ቢጠቀምም ከእግዚአብሔር ዘንድ ግን ቅሥፈትን አስተናግዷል፡፡
አንዳንድ ሰዎች አውናን የተቀሠፈው ዘሩን ከማሕፀን ውጭ በማፍሰሱ ሳይሆን ራስ ወዳድነት በተሞላው ክፉ ተግባሩ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ግን ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ አውናን ዘሩን ከማሕፀን ውጭ በማፍሰሱ እርግዝና እንዳይፈጠር በፈጣሪ ሥራ ስለገባ እና ዘሩን ያለ ቦታው ስላፈሰሰ ነው የተቀሠፈው፡፡ ወዳጆቼ አንድ ወንድ ከሚስቱ ጋር በሩካቤ ሥጋ ጊዜ ዘሩን ከማሕፀን ውጭ ቢያፈስ እና ሌላ ሰው ደግሞ ሚስቱን የእርግዝና መድኃኒት ውሰጂ ብሎ ወይም ሚስቱ የእርግዝና መከላከያ ወስዳ በሩካቤ ሥጋ ጊዜ ግን ዘሩን በማሕፀንዋ ውስጥ ቢያፈስ ዘሩን ከማሕፀን ውጪ ካፈሰሰው ሰው ጋር ልዩነቱ ምንድን ነው? መቼም ዘሩን ከማሕፀን ውጪ ያፈሰሰውን ኮንነን እንዲሁም ዘሩን የወሊድ መቆጣጠሪ በወሰደች ሴት ማሕፀን ውስጥ ያፈሰሰውን ልክ ነው ልንል አንችልም፡፡ ዘሩን በማሕፀን ያፈሰሰውን ሰው ምናልባት ዘሩን በተገቢው ቦታ ማፍሰሱን ነው የምናየው እንጂ ቀድሞ ዘሩ ልጅ እንዳይሆን የተጠቀሙትን የወሊድ መቆጣጠሪያ አናስብም፡፡ አውናን በራሱ የልምድ መንገድ እርግዝናን ስለተከላከለ ተቀሠፈ፡፡ እኛ ደግሞ በሰው ሠራሽ ዘዴ እርግዝናን ብንከላከል ጥፋት አይደለምን?
ወዳጆቼ የትኛውንም የወሊድ መቆጣጠሪያ ስንጠቀም መድኃኒቱ የወንድና የሴቷን ዘር እንዳይዋሐድ፣ በማሕፀን ግድግዳ ላይ ጸንቶ እንዳይቀመጥ እና እንዲመክን/እንዲፈርስ ያደርገዋል፤ ይህ ድርጊት ከአውናን በምን ይለያል? ይህን መሰል ድርጊት ፍትሐ ነገሥ ‹‹መጀመሪያው ግን ስለ ጋብቻ የሆነው መጀመሪያው ፈቃድ አስቀድመን እንዳስረዳን ዘርን ለመተካት ካልሆነ በቀር አይጸናምና፡፡ ዘርንና የሚመስለውን ከማራቅ ጋራ እንግዲህ ሚስት ማግባት እርሱን የሚፈልጉት የማይገኝበት ትሆናለች፡፡ እንዲህ ከሆነ ለሚያገባ ሰው ሚስት ማግባትን መተው ይገባዋል›› ይለናል፡፡ /ፍት.ነገ አንቀ 24÷927/ ይህ ማለት ዘሩን ከማሕፀን ውጪ እያፈሰሰ እና በሰው ሠራሽ መንገድ ልጅ እንዳይወለድ የሚያደርግ ከሆነ ባያገባ ይሻላል ማለቱ ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እኛ የሰው ልጆች ወደ ፊት እርግዝና መከላከያ እንደምንጠቀም አውቆ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜ ላይ ‹‹ለተፈጥሯቸው ልጅ እንዳይገኝ እነሆ ይጥራሉ፡፡ ይሄስ ካሉት መታጣት ይከፋል፡፡ ይህም ክፋት ያሉት ይታጡ ዘንድ ነው፡፡ ይህም ዘርን አውጥቶ በማይሆን ቦታ ስለማፍሰስ ይሆናል፡፡ ፅንስንም ስለ መከልከል ሥራይ በማድረግ ነው›› ብሎናል፡፡ ወዳጆቼ እዚህ ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ‹‹ፅንስን ስለ መከላከል ሥራይ በማድረግ›› ብሎ የገለጠው አሁን ፅንስን ለመከላከል መድኃኒት ለምንውጥ እና መርፌ ለምንወጋ ሰዎች ቀድሞ በመንፈስ ቅዱስ መገለጥ የጻፈልን ነው፡፡ ‹‹ሥራይ›› የሚለውን ቃል የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ›› ‹‹የሚዋጥ መድኃኒት፣ የሚላመጥ፣ የሚጠጣ፣ የሚቀባ›› በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ስለዚህ ፅንስን ለመከላከል ሥራይ ወይም መድኃኒት መውሰድ/መዋጥ የሚገባ እንዳልሆነ ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ እዚህ ላይ ልብ ልትሉት እና በአግባቡ ልትጠቀሙበት የሚገባው፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሠራችልን አጽዋማት እና በዓላት ካወቅንባቸው በራሳቸው የወሊድ መከላከያም ናቸው፡፡ ምክንያቱም በአጽዋማት እና በበዓላት ወራት እና ቀናት ከሩካቤ ሥጋ የምንታቀብባቸው ስለሆኑ በትክክል ከተጠቀምንባቸው ልጆችን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባሰብነው መልኩ እንወልዳለን፡፡ ችግሩ ግን አጽዋማትንና በዓላትን እየሻርን ሩካቤ ሥጋ ስለምንፈጽም ልጅን በአናት በአናቱ ልንወልድ እንችላለን፡፡ አስኪ አስቡት የእርግዝና ወራት፣ ሰባቱ አጽዋማት፣ የአራስነት ወራት፣ ዓርብ ረቡዕ፣ እሑድ ቅዳሜ፣ የሴቶች የወር አበባ ቀናት፤ እነዚህ ከታቀብንባቸው እና በፈቃድ ቀናት ሩካቤ ሥጋ ብንፈጽም ‹‹ያለ ዕቅድ እና ድንገተኛ እርግዝና›› እያልን ከምንሳቀቀው ሰቆቃ ነፃ እንሆናለን፡፡
ይቀጥላል
በ አቤኔዘር ዘተዋሕዶ 🙏