
13/10/2024
መደመር ማለት ምን ማለት ነው ......❓
መደመር ኢትዮጵያን በሁሉም መስኮች የተገኙ ስኬቶችንም ሆነ ችግሮች ሀገራዊ አውድን መሠረት አድርገን ችግሮቻችንን እንዴት ልንፈታ እንችላለን የሚለውን ጥያቄ መልስ ለማመላከት ያለመ ሀገራዊ ዕሳቤ ነው። ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታንና የሰውን ልጅ ተፈጥሮን ያገናዘበ ለሀገር በቀል ችግር ሀገር በቀል መፍትሄ አስፈላጊ በመሆኑ ያጋጠሙንን ችግሮች ለማረም የተነደፈ ሀገራዊ የመፍተሔ ሃሳብ ነው፡፡ በመሆኑም መደመር የሰው “ልጆችን” ፍላጎትና አቅም በማለት በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ በማለት በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ ቀጥተኛ ፍላጎቶች ራስን ከጥፋት መከላከልና ማቆየት ሲሆኑ ተዘዋዋሪ ፍላጎቶች ደግሞ ስጋዊ፤ መልካም ስም እና ነጻነት ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ መደመር የሰው ልጆች አቅም ነጻ ፍቃድ አላቸውም የላቸውምም ብሎ ያምናል፡፡
መደመር የሰው ልጆችን የብቸኝነት ጉድለት የሚለካው በፉክክርና በትብብር መሀል ሚዛን መዛባት እንዲሁም ካለንበት አካባቢ ጋር ግንኙነት መቋረጥ ወደ ቁልቁል እድገትና የህልውና አደጋ ውስጥ ያደርሳል ብሎ ያምናል፡፡ ይህን የብቸኝነት ጉድለት ለመሙላት መፍትሄው መደመር ነው፡፡ መደመር የምልዑነት ጉዞ ነው፣ መንገዱም ሁሉንም ተደማሪዎች አቅምና ፍላጎት በመሰብሰብ በማከማቸት እና በማካበት ሁለንተናዊ ብልጽግና ማምጣት ነው፡፡ የመደመር እሳቤ ዋነኛ አላማው በሀገራችን የተሰሩ መልካም የፓለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችን ጠብቆ ማቆየት የተሰሩ ስህተቶችን ማረም እና የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት በማሳካት ሀገራዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ነው፡፡ መደመር ምልዑ መሆን የሚችለው የመደመር አምዶች የምንላቸው ነገሮችን በሙሉ እይታ በመረዳት፤ ለአንድ አላማ በጋራ መቆም፤ የጋራ ሀገር መገንባትና ተባብሮ ለመኖር የሚመች ስርአት መዘርጋት ናቸው፡፡
የመደመር መሰረታዊያን የተደማሪዎች ተነሳሽነት፤ ነገሮችን ሚዛን መጠበቅና የጋራ ግብ ይዞ መስራት ሲሆን የመደመር ግብ የዜጎችን ክብር በማረጋገጥ ሀገራዊ እንድነትን በማስጠበቅ የኢትዮጲያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ነው፡፡ በነገሮች ላይ እኔ ብቻ ነኝ ልክ የሚል አስተሳሰብ፤ የተበጣጠሰ እይታ መኖር፣ በትላንት ወይም በዛሬ ላይ መታከክና የለውጥ ሀሳቦችን አለመቀበል የእንቢተኝነት አስተሳሰብ ሲሆን በሌላ በኩል ሁሉን ነገር ሳያላምጡ የሚውጡ አድርባዮች መኖር እንዱሁም ሙያን መናቅ የመደመር የአስተሳሰብ እንቅፋቶች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ሌብነት እና ልግመኝነት ወይም አዲስ እውቀት ለማወቅ ተነሳሽነት አለመኖር የመደመር የተግባር እንቅፋቶች ሲሆኑ የእሳቤውን በተግባር ለመተርጎም በእንቅፋትነት የተለዩ ጉዳዮችን ማረም የሀገርን ሁለንተናዊ ብለፅግናን የማረጋገጥ ጉዞ የሀይል አሰላለፍ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡