10/05/2026
ከ95 ዓመት በኋላ አዲስ ታሪክ ሊጻፍበት የተቃረበው 264ኛው ኤል ክላሲኮ
**************
በ35ኛ ሳምንት የስፔን ላሊጋ፣ ዛሬ ሁለቱ የሀገሪቱ ታላላቅ ክለቦች የሚገናኙበት ታላቅ ጨዋታ ይጠበቃል። ሊጉ ሊጠናቀቅ የአራት ጨዋታዎች ዕድሜ ብቻ በቀረበት በዚህ ወቅት፣ በመሪው ባርሴሎና እና በሁለተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ሪያል ማድሪድ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት 11 ደርሷል።
ሪያል ማድሪድ ከዚህ የነጥብ ልዩነት ተነስቶ ዋንጫውን የማንሳት ዕድሉ ከመርፌ ቀዳዳ የጠበበ ቢሆንም፣ ቢያንስ በታሪካዊ ተቀናቃኙ ተሸንፎ ዋንጫውን ሲነጠቅ ማየት አይፈልግም። ባርሴሎና በበኩሉ ይህንን አጋጣሚ እንደ ተጨማሪ ዕድል በመጠቀም፣ ሪያል ማድሪድን አሸንፎ ዋንጫውን በገዛ ሜዳው በማረጋገጥ ለደጋፊዎቹ ልዩ ስጦታ ለማበርከት ወደ ሜዳ ይገባል።
ምሽት 4 ሰዓት ላይ በካምፕ ኑ በሚደረገው ጨዋታ፣ ባርሴሎና አንድ ነጥብ ብቻ ካገኘ የ2025/26 የውድድር ዓመት የላሊጋው አሸናፊ መሆኑን በይፋ ያረጋግጣል። በመሆኑም ሪያል ማድሪድ ይህ ሲሆን ላለማየት ዛሬ ወደ ካታላን የሚያመራው የማሸነፍ አማራጭን ብቻ በመያዝ ነው።
ሎስ ብላንኮዎቹ ከውጤት ቀውስ ባለፈ፣ በሰሞነኛው የፌደሪኮ ቫልቨርዴ እና የኦሬሊን ቹአሜኒ ግጭት ምክንያት በመልበሻ ክፍል ውስጥ በተፈጠረ አለመረጋጋት እየተፈተኑ ይገኛሉ። ይህ የቤት ስራቸው ደግሞ ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጉት ጨዋታ የባርሴሎናን ፈተና ይበልጥ ከባድ ያደርግባቸዋል።
በኤል ክላሲኮ ታሪክ የላሊጋው ዋንጫ አሸናፊ የተለየበት ጨዋታ እስካሁን አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ዛሬ የሚደረገው 264ኛው ኤል ክላሲኮ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ የዋንጫው ባለቤት የሚታወቅበት መርሃ ግብር ሊሆን ይችላል። ከ95 ዓመት በፊት ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ሁለት አቻ ተለያይተው ማድሪድ የዋንጫው አሸናፊ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ፣ ባለፉት ዘጠኝ አስርት ዓመታት ውስጥ ይህ ታሪክ አልተደገመም።
በምሽቱ ጨዋታ ላሚን ያማል በጉዳት ከስብስቡ ውጭ ሲሆን፣ የራፊኛ መመለስም እስካሁን አልተረጋገጠም። በማድሪድ በኩል ደግሞ ኪሊያን ምባፔ ባጋጠመው ጉዳት መሰለፉ አጠራጣሪ ሆኗል። ሆኖም ቲቦ ኮርቱዋ ከጉዳቱ ተመልሶ በምሽቱ ጨዋታ በቋሚነት የመጀመር ዕድሉ ሰፊ ሆኗል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ