13/09/2025
ልታስወርደው ከጫፍ ደርሳ በነበረ ልጇ የምትጦረው የክርስቲያኖ እናት
ማርያ ዶሎሬስ ዶስ ሳንቶስ አቬዬሮ በዓለም ከፍተኛ ተከፋዩ ኳስ ተጫዋች የክርስቲያኖ ሮናልዶ እናት ናት፡፡ ልጇ ዓመታዊ ገቢው ከ200 ሚልዮን ዶላር ከተሻገረ ውሎ አድሯል፡፡
የማርያ ትናንት ጥሩ አልነበረም፡፡ ህይወት በብዙ የጨቆነቻት እንስት ናት፡፡ ከመጠጥ አፍቃሪውና አትክልተኛው ባለቤቷ ጆሴ ዲኒስ አቪዬሮ ጋር ሆና በብዙ ተፈትና አልፋለች፡፡
ሮናልዶን ጨምሮ የአራት ልጆች እናት ናት፡፡ እነሱን ለማሳደግ በፅዳትና በምግብ አብሳይነት ስራ ውስጥ አልፋለች፡፡ ይሄ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ሮናልዶ በማህፀኗ ባለበት ዘመን ታሪካዊ ስህተት ልትሰራ ከጫፍ ደርሳ እንደነበር ታወሳለች፡፡ ድህነትና ለተጨማሪ ልጅ ዝግጁ አለመሆን ደግሞ ዋንኛ ምክንያቷ ነበሩ።
ዛሬ ላይ ያ ከማስወረድ ጫፍ በተአምር የተረፈ ልጇ አንቀባሮ ያኖራታል፡፡ በልጅ ልጆች ተባርካ 70 ዓመታትን ከኖረችባት ምድር ያጣችውን ህይወት በማካካስ ላይ ናት፡፡
ልጇ ክርስቲያኖ ራሱም አንቺ ልታስወርጂኝ ብትፈልጊም አሁን ሁላችሁንም የምደግፋችሁ እኔ ነኝ ሲል ሁኔታውን በቀልድ መልክ ያነሳዋል ሲል TNT sports ዘግቧል፡፡
ከድህነት ህይወት ተነስቶ ዛሬ ላይ ከሁለት መቶ ሚልዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ደሞዝ ተከፋይ መሆን የቻለው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአርባ ዓመቱ ብዙ ድሎችን መቀዳጀት ችሏል፡፡
የአምስት ጊዜ ባላንዶር አሸናፊ፣ አራቴ የወርቅ ጫማ ተሸላሚ፣ የ12 ጊዜያት የዓመቱ ምርጥ ተጫዋችና ሌሎችም ድሎችን ማጣጣም የቻለ የዓለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ነው፡፡ ሰሞኑንም ለአራት የተለያዩ ክለቦች መቶ ጎሎችን በማስቆጠር አዲስ ታሪክ መጻፍ ችሏል፡፡
በዳግማዊት ግርማ አለሙ