
02/02/2025
የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ምርጫ እየተከናወነ ነው
ጅግጅጋ ፤ ( የሶመብኤ ጥር 25/2017 አ.ም) የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ምርጫ በግልፅ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን የፓርቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
ብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን ከጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በማካሄድ ላይ ነው::
የጉባኤውን ሶስተኛ ቀን ውሎ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ የሰጡት የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ከማለዳው ጀምሮ የአመራር ምርጫ ሲካሄድ መዋሉን ገልጸዋል።
በዚህም በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን በከፍተኛ የድምፅ ብልጫ ለፓርቲው ፕሬዝዳንት መምረጡን ተናግረዋል።
አቶ አደም ፋራህና አቶ ተመስገን ጥሩነህ ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ሆነው በከፍተኛ ድምፅ መመረጣቸውን አንስተዋል።
ፕሬዝዳንቱና ምክትል ፕሬዝዳንቶቹ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ቃለ መሃላ መፈጸማቸውንም ነው ያነሱት።
ጉባኤው በከሰዓት ክፍለ ጊዜው የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ምርጫ በማካሄድ ላይ ነው ብለዋል።
በአዲሱ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ቀድሞ የማዕከላዊ ኮሚቴ የሚለው አወቃቀር አሁን የብልጽግና ምክር ቤት በሚል መተካቱን ተናግረዋል።
በአዲሱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀርቶ የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ምርጫ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።
በምርጫው በርካታ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎች ነጻ፣ ገለልተኛና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እጩዎችን ጠቁመው ድምጻቸውን እየሰጡ እንደሚገኙም አንስተዋል።
ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የምክር ቤት አባላት መርጫው ውጤት ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን አንስተው፥ በመቀጠል የፓርቲው ኢንስፔክሽንና የስነምግባር ኮሚሽን እንዲሁም የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እንደሚከናወን አንስተዋል።
የድምፅ አሰጣጡ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ ድምጽን ለመስጠት በሚያስችል መልኩ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
ጉባኤው የብልጽግና የሀሳብ ልዕልና የተገለጸበት እና የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ እየጎለበተ መምጣቱ የታየበት ነው ብለዋል።
እስከሚቀጥለው ጉባኤ የሚተገበሩ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ይፋ እንደሚደረጉም ገልጸዋል።