
18/08/2025
ከ56 ሺህ ቶን በላይ የቅመማ ቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል - ክልሉ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዘንድሮው ዓመት ከ56 ሺህ ቶን በላይ የቅመማ ቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በዚሁ ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በክልሉ የቅመማ ቅመም ሰብሎች በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች አንዱ የሸካ ዞን ነው።
በዞኑ የኪ ወረዳ ህብረት ፍሬ ቀበሌ ከ400 ሄክታር በላይ በሆነ ማሳ ላይ እርድ እየተመረተ ይገኛል።
በቀበሌው "ይቢ" ተብሎ በሚጠራው መንደር የሚገኙ 63 አርሶአደሮች ምርቱን በኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴ በማልማት ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
አርሶ አደሮቹ ለማሳቸው የሚያደርጉት እንክብካቤ እና የሚጠቀሙት ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ለምርታማነቱ አይነተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በየዓመቱ እየጨመረ የመጣውን የቅመማ ቅመም ምርት እሴት ጨምረው ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢ ማሽኖች እንደሚያስፈልጉ አስረድተዋል።
የሸካ ዞን ግብርና ፣ አካባቢ ጥበቃ እና ህብረት ሥራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አዕምሮ ደሣለኝ ከአርሶ አደሮቹ የቀረበው ጥያቄ ተገቢ መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በክልሉ ከ56 ሺህ ቶን በላይ የተለያዩ የቅመማ ቅመም ምርቶች ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ለኢቢሲ ተናግረዋል።
የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት ለዘርፉ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተመልክቷል።