25/08/2026
አስቸጋሪውን የአባይ በረሃን በእግር! ከፍኖተ ሰላም እስከ አዲስ አበባ የተደረገው ጉዞ!
አስቸጋሪውን የአባይ በረሃን በእግር! ከፍኖተ ሰላም እስከ አዲስ አበባ የተደረገው ጉዞ!
የዙምራ እና የአጋሮቹ ጉዞ ፍኖተ ሰላም ላይ አላበቃም፤ ይልቁንም በጽናት የተሞላ ሌላ አዲስ የእግር ጉዞ ተጀመረ። ከፍኖተ ሰላም ተነስተው በባዶ እግራቸው ያደረጉት ረጅም ጉዞ በድካም ቢታጀብም፣ ደብረ ማርቆስ ደርሰው አደሩ። የመኪና እጦት አስገድዷቸው በደርግ አደባባይ ላይ ሁለት ሌሊቶችን ካሳለፉ በኋላ፣ በሶስተኛው ቀን ጉዟቸውን በእግር ወደ ሉማሜ ቀጠሉ። ሰውነታቸው ቢደክምም፣ እግሮቻቸው ቢቆስሉም፣ በልባቸው ውስጥ የሰነቁት ትልቅ ህልም ግን የጉዟቸው ዋና ጉልበት ነበረ።
ከሉማሜ ተነስተው በዝናብና ቅዝቃዜ ተፈትነው ወጀልን ካለፉ በኋላ ደጀን ደረሱ። በማለዳውም መኪና ስላላገኙ፣ አስፈሪውንና አስቸጋሪውን የአባይ በረሃ ቁልቁለት በባዶ እግራቸው እየተንደረደሩ መውረድ ጀመሩ። በዚህ ሁሉ መከራ መካከል ግን ትልቁ እንቅፋት ከፊታቸው ተደቀነ፤ ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ አልያዙም። ያለ መታወቂያ ደግሞ የአባይ ኬላን ማለፍ አይቻልም። ጭንቀቱ በረታ፤ ነገር ግን ተስፋ ባልቆረጡት በእነዚህ መንገደኞች ፊት ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። ሁላቸውም እጃቸውን የዘረጉለት የወታደር መኪና ቆሞ ጫናቸው፤ ያለ ምንም መታወቂያም የበረሃውን ጥብቅ ኬላ በሰላም አሳለፋቸው።
ሾፌሩ በጉሐ-ጽዮን እና በገብረ ጉራቻ መካከል በሚገኝ የገጠር መንደር ላይ አቆያቸው፣ በነጋታውም “እወስዳችኋለሁ” ያለውን ቃሉን ጠብቆ ተመለሰ። እንጦጦ የወታደር ካምፕም አደረሳቸው፣ የካምፑ ሃላፊም ለምን አመጣህ በማለት ሌላ መኪና አስመጥቶ በመጨረሻም አዲስ አበባ መርካቶ አደረሳቸው።
ይቀጥላል...
ሙሉ ቪዲዮውን ለመመልከት እና ሰብስክራይብ ለማድረግ https://youtu.be/yqwnX923Rdc