18/05/2026
መንገድ አልባው መንገደኛ ህዝብ (Untrodden Passengers)
የሀገሬ ኢትዮጵያ ጉዳይ በያዙኝ—ልቀቁኝ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች መወጠር ያሳስበኛል ። ነገር ግን ሳይማር ያስተማረኝ ማህበረሰብ በየዘመኑ በሚፈራረቁ መንግስታት ብሎም ከአብራኩ ክፋይ ተወካዮቹ መንዝ ምን አተረፈ? በዞን፡ በክልል እና በፌደራል ደረጃ ሃላፊነት(ስልጣን) ሲይዙስ ለምን ጀርባቸውን ሰጡት? የሚሉ የህዝብ ጥያቄዎች ደግሞ የበለጠ እረፍት ይነሱኛል። የመንዝ ህዝብ ከዜሮ ድምር መሰረተ ልማት ተጠቃሚነት ፈቀቅ ብሎ ቢያንስ ወጥቶ የሚገባበትን አንዲት የመንገድ መሰረተ ልማት አንስቶ በሰለጠነ መንገድ ህዝብን ማንቃት ተገቢም ሞራላዊ ግዴታም እንደሆነ ይሰማኛል።
በመጋቢት 2010 አ.ም የጣርማበር ሰፌድ ሜዳ ሞላሌ ወገሬ መንገድ ጨረታ ወጥቶ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ሲያሸንፍ ፕሮጀክቱን በ 1.9 ቢሊዮን ብር እና በ ሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ሊያስረክብ ነበር፡፡ መንገዱ ከአዲስ አበባ በ 200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ በሁላችንም ዘንድ ከፍተኛ እምነት ነበረ፡፡ ሆኖም በተፈጠሩ መጓተቶች ቀጥሎም በፌደራል መንግስቱና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል በተፈጠረው ጦርነት ከዚያም በኋላ እሱን ተከትሎ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የመንገዱ ፕሮጀክት ምንም ተስፋ የማይጣልበት ደረጃ ሊደርስ በቅቷል፡፡
አንብበህ ሸር ብታደርገው ጠቀሜታው እንድታነብ ላስተማረህ ክንደ ብርቱው የመንዝ ህዝብ ነው። የፌስቡክን ተፀዕኖ የምታቃልል ተላላ እንዳትሆን
የመንዝ የአስፓልት መንገድ በተመለከ
1. ለመላው_የመንዝ_ህዝብ
"የዘገየ ፍርድ እንደቀረ ይቆጠራል (Justice delayed justice denied)" የሚለው የሰው ልጆች ሁሉ የሚጋሩትን ጥሬ ሀቅ መሰረት አድርገን ስንመለከት በዘመናት ጥያቄ የመልስ ብልጭታ ለታየበት የመንዝ መንገድ ግንባታ ስለይሁንታው ቄጠማ ጎዝጉዘህ ሊሰራልህ ነው የሚል ነጋሪት ተጎስሞልህ በተስፋ ስትጠብቅ ይሄው ቀኑን ቀን እየበላው የመንገዱ የስራ እንቅስቃሴ ቦግ እልም ብሎ ከነጭራሹ እልልልም ብሎልሃል ።
እንኳንስ መንዝን ያህል ለኢትዮጵያ የታሪክ መሰረት መደላድል የጣለ የታሪክ ቤተ መዘክር (ለዚህም አገላለፅ ያልተፃፉትን እንኳን ትተን በኢትዮጵያዊያን ፀሀፍትና በሌሎችም የተሰነዱ የዘመናት ታሪክ በአራቱም መዓዘን በወንዱ ወይ በሴቷ ከመንዝ የዘር ግንድ ያልተገናኘ ነገስታትንና ታላላቅ የትናንት ባለውለታወችን ማግኘት አዳጋች ነው)። ታሪክ ለዛሬ መረሰት መሆን ሲገባው መንዝን በተመለከተ ግን መንዝና አካባቢው ያው እነ ስብስቴ ነጋሲ ክርስቶስ ወረደ ቃል እንዳስቀመጡት መገኘቱ ለዘመኑ ትውልድ ‘አንገት የሚያስደፋ ፊትም የሚያስቀልስ‘ ነው። ይህን ጥሬ ሃቅ በተበታተነ መልኩም ቢሆን የተለያዩ ትንታግ የመንዝ ልጆች በተለያየ መልኩ ጥያቄ ሲያነሱ ይታያሉ። ቅሉ ጥያቄዎቹ መፍትሔ አላገኙም እንጂ። እናም ምርትህን ሸጠህ ለምትሸምተው ሸቀጥ ደብረብረሃን ደርሶ ለመመለስ ከምትጠየቀው ወጭ በላይ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ካንዱ ጥግ ወደሌላ ጥግ ስትላጋ ውለህ፣ አቧራ ጠግበህ አፈር መስለህ ሁለት ሰዓት በማይፈጅ አጭር ርቀት ግማሽ ቀን በቅጥቅጥ መኪና ወንበር ላይ ስትዘል ትውላለህ። እና አንዲት ‘የአሮጊት መቀነት‘ የምታክል የመንገድ ፕሮጀክት በጥራት ሰርቶ ለማስረከብ ይህን ያህል መተሻሸት ምን ይሉታል? እንግዲህ አንተም አይጠፋህ — ‘ዋ‘ በል። ካረረም ይመራል ካልበሰለም ያቅራል በላቸው።
2. ለመንዝ አሽከርካሪዎች ማህበር (Menz Drivers Association)
የመንዝ መልክዓ ምድር ወጣ ገባ መሆን ለተሽከርካሪና ለአሽከርካሪ ፈተና ስለመሆኑ ለአንተ አልነግርህም። ድምፅህ ከፍ ብሎ እንዲሰማ ማህበር አለህ? መቼም የለኝም እንደማትለኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ፅ/ቤትህ ደበረብረሃን ሆኖ የመንዝን የመንገድ የስራ እንቅስቃሴ በየዕለቱ የመገምገምና ለመታዘብ እንዲሁም ቅሬታህንም በተደራጀ መልኩ ለሚመለከተው ሁሉ በማድረስ ተቋራጩንም ይሁን የአካባቢ ተወካዮች ላይ ግፊትና ጫና በመፍጠር ቢያንስ በማና‘ለብኝነት በህዝብ የሚሳለቁትን ፈር ማስያዝ ይጠበቅብሃል። ስለዚህ አሽከርካሪ መሪ ነውና የአንተ የቀን ከቀን ስቃይም ይሁን ምቾት የሚወሰነው እንደ መንገዱ ጥራትና ምቾት በመሆኑ ለመብትህ ተደራጅተህ ታገል፣ ጠይቅ ተጋፈጥ። ካንተ በላይ መንገደኛ የለምና ስለመንገድ አምባሳደራችን አንተ መሆን ይጠበቅብሃል።
3. መንዝ ያበቀለህ ከቀበሌ እስከ ፌደራል የስራ እርከን ላይ ያለህ በሙሉ
የዘመናት ጥያቄ በየመድርኩ ‘ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ‘ ንትርክ ትተህ የመፍትሄ ሰው ለመሆንና በያለህበት የስራ ዘርፍ በተናበበ መልኩ ያላሰለስ ጥረትና ግፊት ብታደርግ ለወቅቱ አንገብጋቢ የመንገድ ግንባታ ፍጥነትና ጥራት የመከታተል፣ የመተቸትና ፊትለፊትም የመጋፈጥ አደራ የመንዝ ህዝብ ሰጥቶሃል። ልብ በል ‘አውራ ዶሮ በቆጡ ንጉስ ነው‘ ባለህ አቅም በመቃወም ልክፍት ሳይሆን በመሰረታዊ ህፀፆችና መፍትሔዎቻቸው ጥያቄህን ገፍተህ አቅርብ: ተደራጅተህ ነገርህ ይሰማ። ያንተን አካባቢያዊ ጥያቄ ከማዶ ሰዎች መልስ መሻትህ ውሃ አይቋጥርምና ተወካይወችህን ሲሰሩ በርቱ በል: ሲያሾፉ ቆንጠጥ አድርግ። በጣም ካላገጡ ገለል ማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀው የሁነቶች መስተጋብር ነው። በልቶ ማደር ከቁምነገር የሚቆጠረው አርሶ የሚያበላህን የመንዝ ገበሬ ከፍሎ የሚጓዝበት የማይጎረብጥ መንገድ ስትሰራለት ብቻ ነው።
4. ለአራቱም የመንዝ ወረዳዎች የህዝብ ግንኙነት ፅ/ቤቶች
እናንተ ይህን የታሪክና የሃይማኖት ቦታዎች መነሻም መድረሻም የሆነን ምድር፣ የአድባራትና ገዳማት ባለዕድል የሆነን አካባቢ እንዲሁም ከደዌው ለመፈወስና ድህነት ለማግኘት ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘን ለሚጎርፈው ምዕመናን ነገም እንዲመለስ እልፍ ሲልም አማኙ ቀስ በቀስ ጎብኚ እንዲሆን የእናንተ መስሪያ ቤቶች ስለመንዝ መንገዶች ጥራትና ፍጥነት ምን አሉ? ከየወረዳው የተውጣጣ የመሀንዲስ ቡድን በእናንተ አነሳሽነት ቦታዉ ድረስ በመጓዝ የመተንተንና የማስተንተን ሀላፊነትስ የማነዉ? የወረዳ አስተዳዳሪዎችንስ ከተወቃሽነት ለማትረፍ እናንተ የህዝብ ጆሮና አይን መሆን የለባችሁም? የተለያዩ ሚዲያዎች እንዲጎበኙት ከማድረግ ባሻገር ቢያንስ በየ15 ቀኑ ለህዝብ ሪፖርት ማድረግ ከባድ ነውን? ዞሮ ዞሮ የማይናቅ ቦታ ላይ ሆናችሁ ታይቶ የጠፋውን ፕሮጀክት አንሱት ከዛም ያልበሰለ አስፓልት ስታስመርቁ እንዳናይ አደራ ለማለት ነው። ትልቅ ሃላፊነት ያለባችሁ መሆናችሁን ተገንዝባችሁ ታሪካዊ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ፡፡
5. ለባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤት
እመጓ ኡራኤልን የሚያክል ለአለሙ ሁሉ የከበደ ቦታ ይዘህ፡ የመንዝ ጓሳን የመሰለ የተከደነ የቱሪስት መዳረሻ ይዘህ፣ በየቀኑ የሚጎርፍ የዘብር ገብርኤል እንግዳ እያየህ፣ ወይናምባ ገብርኤል ተጓዥ የእምዬ ምኒሊክን ግምጃ ቤት አፍቀራን ካላሳየህ፣ የአርብሃራ መድሀኒዓለምን ድንቅ ተዓምር ሀይማኖታዊ በረከትን ፈልጎ የመጣን እንግዳ ሳይጎረብጠው በየጊዜው ቢመላለስ ያለውን ፋይዳ አስበህ የመንዝን መንገድ የስራ ሂደት መከታተል ለመዘገየቱ ፍጥነትን ለጥራቱም መጠበቅ ደፋ ቀና ማለት የለብህም ወይ? እኔ እንደግለሰብ ይሄን ብያለሁ። አንተስ እነደባለሙያ፣ እንደ ወንበርህ ክብደት፣ እንደ ተጓዥ፣ እንደ አሽከርካሪና ባጠቃላይ እንደ በጎ ሰው አሳቢ ለመንዝ መንገድ ጥራትና ፍጥነት ምን እየሰራህ ነው?
መንዝ በአስተዳዳር እራሱን ችሎ እንዲተዳደርና ከተማ ተመስሮቶ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ፤የፍትህ ተቋማት፤ የአስተዳደር መ/ቤቶች እንዲከፈቱ ከንጉስ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ፈቃድ ተሰጥቶ ስራ የተጀመረው ከዛሬ 65 ዓመት በፊት በ1947 ዓ.ም ገደማ ነው፡፡ የመንዝና ግሼ አውራጃም 7 ወረዳዎችን አቅፎ ዋና መቀመጫው በዚሁ በመንዝ መሃል እንብርት ላይ መሃል ሜዳ ሆኖ ከንጉሱ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ አሁን ያለው ከጣርማበር -መንዝ መንገድ የተሰራው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በ1959 ዓ.ም የመንዝ ጀግኖች አርበኞችን እውቅና ለመስጠትና እግረ መንገዳቸውን የስራ መመሪያ ለመስጠት ወደ መንዝ መሃል ሜዳ ከተማ እና ሞላሌ ሲሄዱ ለእሳቸው የተጠረገ የጠጠር መንገድ ነው፡፡ የመንዝ አካባቢ ለምን ከሌላው በተለየ እንዲህ አይነት በደል ሊደርስበት ቻለ ለሚለው መለስ የሚሆነን የከፋ ሸዋ ጠል ትርክት ስለነበረ ነው የሚለው ትክክለኛ መለስ ይመስለኛል፤ በነገራችን ላይ መንዝ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሸዋ ላይ ያለው የልማት እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ለዛሬው የመንዝን እያነሳን ሰለሆነ እንጂ
ይሄ ህዝብ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ በጠጠር መንገድ ሲገለገል የቆየ እና ዞኑ ካሉት ወረዳዎች ውስጥ ለ5 ወረዳዎች አገልግሎት የሚሰጥ እና ከ7 በላይ ወረዳዎችን የሚያገኛኝ መንገድ ሆኖ እያለ በዚህ ደረጃ ህዝቡ እንዲጉላላ እና ተስፋ ቆርጦ እንዲቀመጥ ለምን አስፈለገ? የመንዝ ህዝብ ለሀገር ግንባታ ከጥንት እስከ አሁን ከአርበኝነት እስከ ወታደርነት ልጆቹን መስዋእት አድረጓል? ይሄ የህዝብ ጥያቄ መፍትሄ ይፈልጋል፡፡ የሚመለከታችሁ የመንግስት አካላት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ተጀምሮ የቆመውን የመንገድ ስራ በተመለከተ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታችሁ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ጥያቄውን ለመንግስት በማቅረብ ከህዝብ ጎን በመቆም ትሰሩ ዘንድ እናሳስባለን ፡፡