
24/08/2025
አሚኮ እሴት እና ባሕል ግንባታ ላይ የራሱን ሚና ተጫውቷል።
ደሴ: ነሐሴ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመት በተለያዩ መርሐ ግብሮች እያከበረ ነው። ይህንንም ተከትሎ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጡማ ሞላ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ባስተላለፉት መልዕክት አሚኮ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በቋንቋው ባሕሉን እና እሴቱን እንዲያስተዋውቅ የአፋን ኦሮሞ ዝግጅት ክፍል በማቋቋም ትልቅ ሥራ እየሠራ ያለ ተቋም ነው ብለዋል።
ከነጣጣይ ትርክት በመውጣት ብሔራዊ ገዥ ትርክት ለመፍጠር የሚሠሩ ሥራዎችን አጉልቶ በማውጣት ሀገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ሲሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚሠሩ የሰላም ሥራዎች ሕዝቡ ጋር እንዲደርስ በማድረግ ረገድ አሚኮ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷልም ብለዋል አፈ ጉባኤዋ።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕል፣ እሴት እና አብሮነት እንዲጠናከር ከማድረግ ባሻገር ከአጎራባች ዞኖች ጋር ያለው ወንድማማችነት እንዲጠናከር በማድረግ ውስጥም ሚናውን እየተወጣ ያለ ተቋም መኾኑን አስረድተዋል።
አሚኮ በቀጣይ የሕዝብ ድምፅ መኾኑን በማስቀጠል በክልሉ የሚሠሩ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ለሕዝቡ ለማድረስ በትኩረት ሊሠራ ይገባልም ብለዋል።