
05/09/2025
ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተወለዱት በመካ የበኒ ሐሸም ሸለቆ ውስጥ በረቢዐል አወል ወር በዕለተ ሰኞ ማለትም እውቁ የታሪክ ተመራማሪ ሙሐመድ ሱለይማን መንሱር ፉሪና የሥነ ፈለክ ምሑራን ማሕሙድ ባሻ እንዳረጋገጡት በወርሃ ኤኘሪል 571 (ዓ.ል) የዝሆኑ ክስተት በተፈጸመ በዐመቱ፣ ኪስራ አኑሽረዋን በነገሠ በአርባ ዐመቱ ነው። ኢብን ሰእድ እንደዘገቡት የነቢዩ ሙሐመድ እናት ስለዚያች እለት ሲገልጹ፦ “ሙሐመድን በወለድኩ ጊዜ ከማሕጸኔ ብርሃን ወጥቶ የሶሪያን አብያተ መንግሥታት በብርሃኑ አደመቀ” ብለዋል።
ነቢዩ እንደተወለዱ እናታቸው ወደ አያታቸው ወደ ዐብድል ሙጦሊብ የብሥራት መልእክት ላከች። አያታቸውም በደስታ ተሞልተው መጡ። ሕጻኑንም ወደ ካእባ ይዘውት ገቡ፡፡ ዱዓ አደረጉለት፡፡ አላህንም ኣመሰገኑ፡፡ ሙሐመድ የሚል ሥም መረጡለት። ይህ ሥም ከዚህ ቀደም በዐረቦች ዘንድ የሚታወቅ አልነበረም። ዐረቦች እንደሚያደርጉት በሰባተኛው ቀን ገረዙት፡፡ እንደተወለዱ ከእናታቸው ቀጥሎ ያጠባቻቸው ሴት ሱወይባህ የተባለች የአቡ ለሐብ አገልጋይ ናት፡፡ አሳዳጊያቸው ነቢዩ ሙሐመድን ከሐሊማ ዘንድ በነበሩ ጊዜ አጥብታቸዋለች።
ሐሊማ ስለ ነቢዩ ሙሐመድ በረከታማነት ድንቃ ድንቅ ታሪኮችን አውግታለች። ኢብን ኢስሐቅ እንዲሀ ማለቷን ዘግበዋል፤ የማሳድገው ልጅ ፍለጋ ከትንሹ ልጄና ከባሌ ጋር በመሆን ከበኒ ሰእድ እንስቶች ጋር ወጣሁ። ዐመቱ የድርቅ ዓመት ነበር። ምንም ነገር አልነበረንም። ቦቃማ አህያ ተፈናጥጨ መጣሁ፡፡ ግመልም ነበረችን። ልጃችን ከረሃብ የተነሳ ስለሚያለቅስ ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ በዓይናችን ሳይዞር ይነጋ ነበር። ጡቴ የሚያጠግብ ወተት አልነበረውም፡፡
ግመሏም የሚታለብ ወተት አልነበራትም፡፡ ግና አንዳች በጎ ነገር ተስፋ እናደርግ ነበር። አህያ እየጋለብኩ ረዥም መንገድ ተጓዝኩ። ድካም አልፈሰፈሰን። መካ ደርሰን የምናሳድገው ልጅ ፈለግን። የአላህን መልእከተኛ ያገኙ እንስቶች ሁሉ የቲም መሆናቸው ሲነገራቸው ሊወስዷቸው ፈቃደኛ አልሆኑም። ምክንያቱም ልጅ የምናሳድገው ከአባቱ በነ ውለታን በመፈለግ ነበር። የቲም ከሆነ ግን፡ “እናቱ እና አያቶቹ ምን ሊፈይዱልን?” እንል ነበር። በዚሀ ምክንያት የቲም መውሰድ አንፈልግም ነበር። አብረውኝ የመጡ እንስቶች በሙሉ የሚያሳድጉት ልጅ አገኙ። ልንመለስ በመዘጋጀት ላይ እያለን ለባለቤቴ፣ “በአላሀ እምላለሁ፣ የማሳድገው ልጅ ሳልይዝ ባዶ እጄን መመለስ ኣልፈልግም። ያን የቲም ልጅ ይዠው እመስሳለሁ” አልኩት። “ይሁን፣ ያዥው። አላህ በረከት ያደርግልን ይሆናል” አለኝ። ሄድኩና ያዝኩት፡፡
እንድወስደው ያስገደደኝ ሌላ ልጅ አለማግኘቴ ብቻ ነበር። ይዠው ወደ ማረፊያችን ተመለስኩ። ከጭኔ ላይ ሳስቀምጠው ጡቶቹ ወተት ያፈሱ ጀመር። እስኪጠግብ ድረስ ጠጣ። ወንድሙም እንደዚሁ እስኪጠግብ ጠጣ። ሁለቱም ተኙ። ከዚያ ቀን በፊት በልጄ ለቅሶ ምክንያት ተኝተን አናውቅም ነበር፡፡ ባለቤቴ ወደ ግመሏ ሲሄድ ጋቷ ሞልቶ አገኛት። አልቦ አመጣና እስክንጠግብ ድረስ ጠጣን፡፡ መልካም ሌሊትም አላለፍን፡፡
ሲነጋ ባለቤቴ፤ “ሐሊማ ሆይ፣ የያዝሽው ልጅ በረከታማ ነው” አለኝ። “በአላህ እምላለሁ፣ እኔም እንደዚያ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ” ኣልኩት። ጉዟችንን ቀጠልን። ከአህያዬ ላይ ከልጁ ጋር ተፈናጠጥን። የሁሉንም አህያ ቀድማ ገሰገሰች። ባልንጀሮቼ ተገረሙ። “የመጣሽበት አህያ አይደለምን? እባክሽን አትሩጭብን” ይሉኝ ጀመር። እኔም፡ “እርሷው ናት” ስላቸው፡ “የገጠማት አንዳች ነገር አለ” ይሉኝ ነበር። ከአገራችን ከበኒ ሰእድ ምድር ደርሰን አረፍን። እንዲያ ያለ ድርቅ አይቼ አላውቅም። ግና ከተመለስን በኋላ (ቤታችን በረከታማ ሆነ)፡፡ ፍየሎች ውለው ሲገቡ ጠግበውና ጋታቸው ሞልቶ ነው። እነርሱን እያለብን እንጠጣለን። ሌሎች ሰዎች ግን ከፍየሎቻቸው ጋት ጠብታ ወተት አያገኙም። የመንደሩ ሰዎች ለልጆቻቸው፡- “አደራችሁን፣ የአቢ ዙአይብ ልጅ (የሐሊማ) ፍየሎች ከሚስማሩበት አሰማሩ” በማለት ያዙ ጀመር። ይህም ሆኖ የነርሱ ፍየሎች ጋት ጠብታ ወተት አይቋጥሩም። የኔዎቹ ግን ጋታቸው ሞልቶ ይፈሳል። በዚህ ሁኔታ የአላህን በረከት እያገኘን ሁለት ዐመታትን አሳለፍን። ልጁም እያደግ ሄደ። ጨዋታው እንደሌሎች ልጆች አይደለም፡፡ ሁለት ዓመት ሲሞላው ጎበዝና ጠንካራ ልጅ ሆነ። ከእናቱ ዘንድ ወሰድነው፡፡ በረከታማ ከመሆኑ አኳያ አብሮን እንዲቆይ ስለፈለግን እናቱን፡ “የመካን ወባ ስለምንፈራለት ከኛ ዘንድ ጥቂት እስኪጎብዝ ይቆይ” ስንል ተማጸንናት። አብሮን እንዲመለስ ፈቀደችልን።
የአላህ መልእክተኛ በዚህ አኳኋን ከበኒ ሰእድ አገር ቆዩ። እድሜያቸው አራት ወይም አምስት ዓመታት ሲሞላቸው ድንቅ ነገር ተከሰተ። ሙስሊም አነስን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ከልጆች ጋር በመጫወት ላይ እያሉ ጅብሪል መጣና ያዛቸው፡፡ ከመሬት ላይም ጣላቸው፡፡ ደረታቸውን በመቅደድም ልባቸውን አወጣው። የተላመጠ ስጋ የሚመስል አንዳች ነገር ከውስጡ አወጣና፡ “ከአንተ ውስጥ የሰይጣን ድርሻ ነው” ካለ በኋላ በወርቅ ሳህን ላይ አስቀምጠ በዘምዘም ውሃ አጠበው። ከዚያም ወደነበረበት ቦታ መለሰው፡፡ ልጆች ወደ እናታቸው ዘንድ እየሮጡ በመሄድ፡ ‹‹ሙሐመድ ተገደለ» ሲሉ ነገሯት። ከነርሱ ጋር ስትመጣ የነቢዩ ፊት ተለዋውጦ አገኘቻቸው። አነስ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፡ “የዚህን ክስተት ፋና ከደረታቸው ላይ እመለከት ነበር።” (ሚንበር ቲቪ)
ምንጭ፡ ረሒቀል መኽቱም
★ ★ ★ Minber TV | EthioSat | 11545 | H | 45000 !