20/10/2025
ሰበር መረጃ
“በግፍ ያጣናው የባህር በር የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መመለሱ አይቀርም” ኮሞዶር ተገኝ ለታ፤ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ
“በግፍ ያጣናው የባህር በር የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መመለሱ አይቀርም” ሲሉ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ ኮሞዶር ተገኝ ለታ አስታወቁ። የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ መመለስ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሰላምና መረጋጋት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ምክትል ባሕር ኃይል አዛዡ ገልጸዋል።
ምክትል አዛዡ ይህን የተናገሩት ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በመከላከያ ዋር ኮሌጅና በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ትብብር “የሁለቱ የውሃ ሥርዓቶችና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ነፃነት፣ የዓባይና የቀይ ባሕር ትስስር እና የአፋር ክልልን ስትራቴጂካዊ ሚና መዳሰስ” በሚል ዐቢይ ርዕስ በሠመራ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ ኮሞዶር ተገኝ ለታ የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን በሀገሪቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ሊኖረው የሚችለው ኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ መዘዝን መረዳት ተገቢ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
“የወደብ ጉዳይ መንግስታዊ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል” ያሉት የባህር ኃይል ምክትል አዛዡ፤ በቀይ ባሕር ቀጣና እየታዩ ናቸው ያሏቸው ጂኦ ፖለቲካዊ ለውጦች ኢትዮጵያ ከቅርብ ባሉት ነገር ግን በውል ካልጠቀሱት ጊዜ ወዲህ በቀይ ባህር ላይ ያላት ጥያቄ ቀዳማዊ ብሔራዊ አጀንዳ ለማድረጓ ገፊ ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል። በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ያለው የሎጂስቲክስ ፍላጎት ለጥያቄው መነሳት አንደኛው ምክንያት መሆኑንም አመላክተዋል።
እንደምክትል አዛዡ ገለጻ፤ የባሕር በር ያስፈለገበትን ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ያሏቸው ነገር ግን በስም ያልጠቀሷቸው ሀገራት በቀጣናው የጦር ሰፈር መገንባታቸው ነው።
“በመሆኑም የጦር ሰፈሮች በቀጣናው መኖራቸው ይዟቸው የሚመጡ ችግሮችን ቀድሞ በመተንበይ፣ በመዘጋጀት፣ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል” ብለዋል።
የወደቡ ጉዳይ ዕልባት አለማግኘት ከቀጠለ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አስተዋጽዖ ማድረጉ የማይቀር መሆኑን በማመለካት አስፈላጊነቱን እና ሊያመጣ የሚችለውን አሉታዊ ውጤትም አስገንዝበዋል።
በሰሜናዊ ሕንድ ውቅያኖስ እና ቀይ ባህር ላይ የሚታዩ ውንብድናዎችንና ግጭቶችን ለመከላከል ጠንካራ የባህር ኃይል አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ ስለመሆኑም ምክትል አዛዡ ተናግረዋል።
የባሕር በር አስፈላጊነትን፣ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን በግፍ መነጠቋን እንዲሁም መመለሱ አይቀሬ መሆኑን ሲናገሩ ምክትል አዛዡ የመጀመሪያው አይደሉም።
በመከላከያ ሚኒስቴር የውጪ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ተሾመ ገመቹ የባህር በር እየጠየቅን ያለነው “ዝም ብለን ከመሬት ተነስተን አይደለም” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ለዚህም አራት ምክንያቶችን የጠቀሱ ሲሆን እነዚህም ኢትዮጵያ ከአሰብ ጋር ያላት ታሪካዊ ትስስር፣ መልካም ምድራዊ ቅርበት፣ የህልውና ጥያቄ እና የጸጥታ ስጋቶች መሆናቸውን መናገራቸው ይታወሳል። ሌሎች ወታደራዊ መኮንኖችም ተመሰሳሳይ አስተያየት ሲያንጸባርቁ መክረማቸው አይዘነጋም።