04/11/2023
"በትምህርት ሴክተሩ የገጠመንን ስብራት አንዱ ለሌላው ከመወራወር ይልቅ እያንዳንዳችን የሚጠበቅብንን በማበርከት ለችግሩ መፍትሔ መሆን ይገባናል" ሲሉ የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ወይንሸት ሞላ ገለጹ
ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት 24/2016 የወላይታ ዞን ምክር ቤት በ2015 የትምህርት ዘመን የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል የተማሪዎች ውጤት እና የትምህርት ጥራት ቀጣይ መፍትሔ አቅጣጫዎች ዙሪያ የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ አካሄደ።
የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ወይንሸት ሞላ የትምህርት ተቋማት ትውልድ የሚገነባባቸው ተቋማት ናቸው በማለት ከገጠመን የትምህርት ውድቀት አንጻር ነገ አገርን የሚረከብ ዜጋን የማፍራት ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን በመገንዘብ የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በትምህርት ሴክተሩ የገጠመንን ስብራት አንዱ ለሌላው ከመወራወር ይልቅ እያንዳንዳችን የሚጠበቅብንን ማበርከት መፍትሔ ልናመጣ ይገባናል ሲሉ ለተሳታፊዎች ገልጸዋል ወ/ሮ ወይንሸት።
በ8ኛና 12ኛ ክፍል የተማሪ ውጤት ለማስተካከል እያንዳንዱ ባለድርሻ የሚጠበቅበትን በመውሰድ ለመፈጸም መግባባት የሚፈጠርበት መድረክ እንደሆነም በመግለጽ ሁላችንም ከተኛንበት መንቃት ያስፈልጋል ሲሉም አብራርተዋል።
የወላይታ ዞን ብልጽግና ረዳት የመንግስት ተጠሪና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ተመስገን አለማየሁ በበኩላቸው የትምህርት ውድቀትን ለማስተካከል ሁሉም ከራስ ጀምሮ እርምጃ እየወሰደ መምራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
የትምህርት ሥራ የተመራበት አግባብ ለውድቀታችን መነሻ ነው ሲሉም ገልጸው ተቆራርጦ የመምራትና ከሴክተሩም ከባለድርሻ አካላትም ቁርጠኝነት ይጠበቃል ብለዋል።
የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ኩማ የትምህርት ውድቀት መነሻው ዓመታትን ያስቆጠረ እና በትምህርት ጥራት ላይ ሥራዎች ባለመሠራታቸው የመጣ ውድቀት ነው ሲሉ ገልጸው ሁሉም የትምህርት አመራር፣ መምህራን፣ ተማሪ እንዲሁም የተማሪ ወላጆች እጅ ለእጅ በመያያዝ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የዘርፉንም ችግር ለመፍታት የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ መደረጉን እንዲሁም በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጁ መጻሕፍት የማዳረስና የትምህርት መሠረተ ልማቶችን ባለድርሻ አካላት በማስተባበር የማሟላት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን በማስረዳት ከረጅም ጊዜ መፍትሔ አኳያ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ሠፊ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል።
የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በክረምቱ ወቅት ከ150 ሚሊዮን በላይ ግምት ያላቸው የህዝብ ተሳትፎ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
የሁምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ፀጋዬ ቀልታ የትምህርት ስብራት እጅግ የከፋ መሆኑ የትምህርት ሥርዓታችን ችግር ያለበት መሆኑን ያመላከተ ነው በማለት ሁላችንም የጋራ ችግርና ውድቀት አድርገን በመውሰድ በፍጥነት ሠርተን መውጣት ይኖርብናል ሲሉ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ሌሎች የትምህርት አመራ፣ የተማሪ ወላጅ፣ እንዲሁም ተማሪ በውድቀቱ ድርሻ ያለው በመሆኑ በጋራ ውይይት ከችግሩ ለመውጣት እየተሠራ እንደሆነም የገለጹት አቶ ፀጋዬ የግብዓት ማሟላት ሥራም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመሥራት ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የሙያ ማህበሩ ከትምህርት አመራሩ ጋር ተባብሮ ይሠራል ያሉት የወላይታ ዞን መምህራን ማህበር ሰብሳቢ ወ/ሮ ባዩሽ ዘውዴ የትምህርት ጥራት ማስጠበቅና የመምህራን መብት ማስከበር የሙያ ማህበሩ ዋናው ተግባሩ እንደሆነ በማብራራት ችግሩ የጋራ ቢሆንም የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሁሉም መምህራን ችግር ፈጣሪዎች ናቸው ባይባልም ችግር ፈጣሪዎች ላይ ተለይቶ እስከማገድ እርምጃ እየተወሰደ እየተመራ እንደሆነ ያብራሩት ሰብሳቢዋ በመሠረታዊ ችግሮቻችን ላይ ተግባራዊ ጥናት እየሠሩ ግብረ መልስ እየሰጡ እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።
ሐጂ ናስር የሱፍ እና አቶ ሚልክያስ ኦሎሎ ከባለድርሻ አካላት የተገኙ ተሳታፊዎች ሲሆኑ እንደሀገርም እንደወላይታም ወድቀናል ሲሉ ገልጸው የኃይማኖት ተቋማት፣ የተማሪዎች ወላጆችም ሆነ መምህራንና ተማሪዎች ድርሻቸውን መውሰድ አለባቸው ብለዋል።
መንግስት መምህራንን የማብቃት ሥራ መሥራት አለበት ያሉት የኃይማኖት አባቶች ትምህርት ቤት የማይሄዱ መምህራን መታረም እንዳለባቸው እና የተማሪ ሥነ ምግባር የማስተካከል ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።
እንደዞን ከተፈተኑ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች 1.66% ብቻ ማለፋቸው ፤ የ12ኛ ክፍል ፈተና ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች 36ቱ(45%) አንድም ተማሪ 50% እና በላይ ያላስመዘገቡ መሆናቸው እንዲሁም እንደወረዳ ካስፈተኑት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ምንም ተማሪ ያላሳለፉ አባላ አባያ፣ ሆብቻ እና ሁምቦ ወረዳዎች መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ መረጃ አመላክቷል።
የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አፈ ጉባኤ ጽ/ቤት ማኔጅመንት፣ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ማኔጅመንት፣የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የወረዳና ከተማ አፈ ጉባኤዎች የኃይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች የመምህራን ሙያ ማህበራት ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የንቅናቄ መድረኩ ተሳታፊዎች ናቸው።