18/06/2025
አንድ እውነት በንግግር ሳይሆን በተግባር ማየት ከቻልክ አንተ ትክክለኛ ተመራማሪ ነህ። እውቀትም እውነትም በትክክለኛው መንገድ ታገኝበታለህ። በንግግርማ ማንኛውም የትናቱ ወጠጤ ራሱን በሰማይ አስቀምጦ አያስነካህም። ከአፉ የሚወጣውን ቃል አልፈህ ወደ ታሪኩ ሲትመጣ ግን ነገሩ ጉም መጨበጥ ይሆንብሃል። በአፈ-ታሪክ የመሸወድ ጊዜ ይብቃህ።
ና! ወደ 50+ ነገሥታት ሀገር ወደ ወላይታ ና! በላይና በታች የሚንጫጫ የጫጩቶች ድምፅ አልፈህ ና! የትናንትናዎቹ አዲስ ጎጆቹን አልፈህ ከጥንት ጀምሮ መሠረቱን በዓለት ላይ ወዳደረገው ቤት ወደ ወላይታ ና!
በአቅራቢያው ካሉት ወገኖች ቀንጨብ ቀንጨብ አድርጋ በመውሰድ ብሔሯንና ባህሏን ገና እየቀረፀች ካለችው ከግልገሏ አልፈህ ብዙኃኑን አቅፈው ቋንቋውንና ባህሉና በልግስና ተሰጥቷቸው በሥልጣኔ ጎዳና ላይ እንዲራመዱ ወዳደረገው ወደ ወላይታ ና!
መጥቼ ምን የተለየ ነገር አያለሁ ትላለህ? ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው። መጥተህ የሚታየው:-
#1. ከሃምሣ በላይ የወላይታ ነገሥታት ታሪክን ፤ የመንግሥታቸውን ሥርዓት ፤ ዲፕሎማሲያቸውን፤ ድንበር ጠባቂ ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ አናሳ ጎሳዎችን በራሳቸው እያጠቃለሉ ድንበራቸውን ያስፋፉ መሆናቸውን፤ ጀግንነታቸውንና ሥልጣኔያቸውን ትመለከታለህ።
#2. ማርጩዋ ታያለህ። ማርጩዋ ምንድ ነው ልትል ትችላለህ። በዱሮ ገበያ ሥርዓት ሰው የተለያየ ዕቃ ይዘው ወደ አንድ ሜዳ በመሰብሰብ ዕቃን-በዕቃ እየቃያየሩ የሚገበያዩበት ሥርዓት ነበር። ይህንን ሥርዓት በማዘመን በአህጉር ቀዳሚ የሆነውን ማርጩዋ የተባለውን የሀገሩ ገንዘብ በማምረት ዕቃን በገንዘብ የመግዛት ዘመናዊ የገበያ ሥርዓት ያመጣ በአፍሪካ ተቀዳሚ ሀገር ወላይታ ነው። በዚያን ዘመን በማርጩዋ ዓለም አቀፋዊ ንግድ እንደሚደረግና አንድ ማርጩዋ በስድስት ዶላር እንደሚመነዘር ታሪኩ ያረጋግጣል። ና ላሳህ!
#3. ታሪካዊና መዝናኛ ቦታዎችን ትጎበኛለህ። ካዎ ጋሮታ(ቤተ-መንግሥታት)፤ ታሪካዊና ከ70,000 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ዋሻዎችን፤ በአፍሪካ ደረጃ ረዥም የተባሉ ፏፏቴዎችን፤ ጦሳ ዛርጵያ(የእግዜር ድልድይ)፤ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሐይቆችን፤ እስከ አጎራባች አፍሪካ ሀገራት ድረስ ተዘርግተው ለሃገራችን ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የሆነውን ጊቤ-3 ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ፤ ተክል ድንጋዮችን፤ ጥንታዊና ታሪካዊ ከተሞችን፤ ሙሉ የወላይታ ህዝብ ጥንታዊ የቤት ቁሳቁሶችንና የጦር መሣሪያዎችን የያዙ ሙዚየሞችን፤ በራሱ ዘመን አቆጣጠር መሠረት አዲስ ዓመትን የሚቀበልበት የጊፋታ በዓልን፤ ወዘተ ትመለከታለህ።
#4. ጥንታዊ የወላይታ ህዝብ ሙዚቃ መሣሪያዎችንና ህዝባዊ ዘፈኖችን ታያለህ፤ትሰማለህም። በአፍሪካ አህጉር ከወፎች ዝማሬ በስተቀር በዜማ የሚከፈት የሰው አፍ ባልነበረበት ዘመን የወላይታ ህዝብ ለሠርግ፤ ለደቦ ሥራ፤ ለልደት፤ ለሙሾ፤ ለበዓላትና ለተለያዩ ጉዳዮች እንደየሁኔታቸው የቃል ግጥም በማዘጋጀት ኩነቶችን በዜማ ይገልፁ ነበር። በዚያ ብቻ ለምን ትደነቃለህ? የኩኔቶችን ዜማ የሚደግፍ ላሁኖች ሙዚቃ መሣሪያዎች መሠረት የሆኑ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ሙሉ ባንድ አድርገው መፍጠራቸውን መቼ ሰማህ? ድንክያ፤ጫቻ ዛእያ፤ኡልዱዱዋ፤ካምባ፤ካራቢያ፤ዲታ፤ እና የመሳሰሉትን በመፍጠር ከዘመን ቀድሞ በመሠልጠን ዜማቸውን በባህላዊ ባንድ ታጅበው ያቀርቡ ነበር።
#5. ጥንታዊ የወላይታ ህዝብ ባህላዊ ልብሶችን ትመለከታለህ። ሃድያ ተብለው የሚጠራው የወላይታ ብሔር ባህላዊ ልብሶች አጠቃላይ ስያሜ በውስጡ አምስት ዓይነት ባህላዊ ልብሶችን የያዘ ነው። አዎ! የወላይታ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ የሠለጠነና ምሁር ህዝብ ነው። ለለቅሶ የሚለብሰውን ለሠርግ አይለብስም። ለሠርግ የሚለብሰውን ለጦር ሜዳ አይጠቀምም። ንጉሥ የሚለብሰውን ህዝብ አይለብስም። ለሁሉ የየራሱ ባህላዊ ልብስ በአምስት ዓይነት በማዘጋጀት ሥርዓት ባለው መልኩ የተጠቀመ ህዝብ ነው። በዚያን ዘመን የወላይታ ብሔር ቀያይረው ስለለበስ የአፍሪካ ምድር ላይ የልብስ ፋብሪካና ሌላ ልብስ የሚጠቀም ብሔር ያለ እንዳይመስልህ! አአልነበረም። ግን ጠቢቡ የወላይታ ህዝብ ልብሶቹን በእጆቹ ሸምኖ በማዘጋጀት ይጠቀም ነበር። ልብሶቹም:-ጉቱማ ሃድያ፣ ሴሬ ሃድያ፣ ጉማራ ሃድያ፣ ፓታላ ሃድያ እና ዱንጉዛ ሃድያ በመባል ይታወቃሉ። ዕድለኛ ከሆንክ ስትመጣ አይተህ ትመሠክራለህ።
#6. ጥንታዊ ቤተ-እምነቶችን ታያለህ። በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ከየትኛውም ብሔር ቀድሞ የክርስቲና እምነት የተቀበለው የወላይታ ህዝብ ነው። ከ700ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማንያን ቤተክርስቲያንን ታያለህ። ከወላይታ ህዝብ የተገኙ አባታችን ሶስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ያረፉበትን መቃብር ታያለህ። በኢትዮጵያ ደረጃ ከሁሉም ቀድሞ የወንጌላውያን አቢያተክርስቲያናት እምነት የተቀበለው የወላይታ ህዝብ ነው። ለአብዘኞቹ የወንጌላዊት ቤተ-እምነቶች እናት የሆነችው የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የተጀመረችው ብሎም ስያሜዋን ያገኘችው በወላይታ እምነት አባቶች ነው። በርካታ ነቢያት ፈጣሪ በሰጣቸው ራዕይ መሠረት የሚንትሪ ቤተ አምልኮ መሥርተው ባሁኑ ጊዜ በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ነፍሳት ወደ ፈጣሪያቸው መንግሥት እንዲቀላቀሉ በማድረግ ላይ ያሉ ታላቅ አገልጋዮች የተወለዱበት ሀገር ወላይታ። በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ኃላፊነት የሚሠሩ ታላላቅ የእስልምና እምነት ተከታዮችና ዕድሜ ጠገብ መስገዶች ያሉበት ሀገር ነው ወላይታ። የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎችን ሙሉ የሚያስተዳድረው ፣ ሰፊ በመንፈሳዊና ማህበራዊ ድጋፎችን በመስጠት የሚታወቀው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያው የደቡብ አካባቢዎች ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታገኛለህ። በሐዋሪያት ቤተ እምነት፣ በአድቫንቲስት ቤተ- እምነት፣ በይሆዋ ምስክሮች ቤተ እምነት ፣ ወዘተ የወላይታ ምድር ተቀዳሚ ናት። መጥተህ ካየህ ከሰማኸው ይበልጣል።
#7. በእንግዳ ተቀባይነቱ፣ በአቃፍነቱ፣በለጋስነቱ፣በጀግንነቱ፣በሥራ ወዳድነቱ፣በጥበቡ፣በታታሪነቱ፣በፈጠራ ሥራዎች፣ በምርምር፣ ወዘተ የሚታወቀውን ታላቁን የወላይታ ህዝብን ታያለህ። በእርግጥ የወላይታ ህዝብና ወላይትኛ ቋንቋ የሌለበት የዓለም ክፍል የለም። ቢሆንም መነሻውጋ በመምጣት የሚታየው ህዝብና የሚትሰማው ወላይትኛ የተለየ ደስታ እንደሚሰጥህ ሙሉ እምነት አለኝና ግድ የለም ና!
#8. መጥተህ የሚትመገበው በዓለም ደረጃ ተወዳጅነትን ያተረፈው የወላይታ ባህላዊ ምግብ። አንተ ብቻ መምጣትህን እርግጠኛ ሁን። የወላይታ ህዝብ ሎጎሙዋ፣ ሱልሱዋ፣ቆጭቆጫዋ፣ ባጭራ፤ሼንደራ፣ፕጫታ፣ ሙቹዋ፣ ፖሻሙዋ፣ ብላንዱዋ፣ Cadhdhiyaa፣ፕላ፣ጉርዱዋ፣ እና ከሁሉም በላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የጥሬ ስጋ አምሮቱን ለማርካት ወደ እኛ እንዲመጡ ምክንያት የሆነውንና በብዙ ዓይነት ዳጣ በተለየ አቀራረብ የሚቀርበውን፤ የወላይታ አምባሳደርም የሆነውን ቁርጥ ሥጋ በቃኝ እስኪትል ድረስ ልመግብህ ተዘጋጅተው እየጠበቀ ነዉ።
ስትመጣ የመንገድ ችግር የሌለበት፤ ስትደረስ የመብራት፣ የንፅህና ውኃ፣ ንፁህ ማረፊያ ሥፍራ፣ የኔትወርክና የነፃ ዋይፋይ ችግር በፍጹም አይገጥምህም። ዛሬ ያገኘህ ወላይታዊ ወንድምህ ሆኖ በሴኮንድ ይግባባሃል። ወደ ቱሪዝም መዳረሻዎች የሚያጓጉዙ ምቹና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ደግሞ እንግሊዘኛን ጨምሮ ከሀያ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራትን ቋንቋዎችን አቀላጥፈው የሚናገሩ አስጎብኚዎች ተዘጋጅተው ይጠብቁሃል። ና!
ግን ትመጣለህ ወይስ ዝም ብለህ አስለፈለፍከኸኝ?
youtube.com/