27/08/2026
የቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የመሪዎች አስተሳሰብ እንዲቀየር ጥሪ አቀረቡ
| በኪጋሊ በተካሄደው "የአፍሪካ የአስተሳሰብ ለውጥ ፎረም" ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት አቶ ኃይለማሪያም አህጉሪቱ እያሳየች ያለችውን እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የፖለቲካ ኢኮኖሚው ከኪራይ ሰብሳቢነት አሰራር ወጥቶ ወደ ልማት ተኮር ስርዓት መለወጥ እንዳለበት አስምረውበታል።
አህጉሪቱ አሁንም ወደኋላ የቀረችው ለልማት በቂ ትኩረት በማይሰጡ የአመራር አካሄዶች ምክንያት መሆኑን የጠቆሙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ለአመራር ለውጥ ትኩረት መስጠትና አዳዲስ አፍሪካውያን መሪዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ ኃይለማሪያም አክለውም የአህጉሪቱን አስተሳሰብ መቀየር በአንድ ጀምበር የሚከናወን ሳይሆን የረጅም ጊዜ ሂደት መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም እንደ አንድ አካል የመፃኢ ጊዜ መሪዎችን ለመቅረጽና ተግባራዊ የለውጥ እንቅስቃሴን ለመፍጠር (African School of Governance) መመስረቱን ተናግረዋል።
አፍሪካን ለመቀየር የፖለቲካና የንግዱ ኤሊቶች ጥረት ብቻውን በቂ እንዳልሆነና የሰፊው ሕዝብ ንቁ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።
በተጨማሪም ችግሮችን ከመዘርዘር ባለፈ አፍሪካውያን የሚመሯቸውን መፍትሔዎች መተግበር ከግል ስኬቶች ወጥተው አስተማማኝ ተቋማዊ ስርዓቶችን መገንባት እንዲሁም ከቋሚ አስተሳሰብ ይልቅ እድገትንና የተጎጂነት ስሜትን ማስወገድ ላይ ትኩረት አድርገዋል።
በዚህ መድረክ ላይ እንደ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የጋናው ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ቶቦ እምቤኪ እና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የተሳተፉ ሲሆን ወቅታዊና የቀድሞ የሀገር መሪዎች፣ የኮርፖሬት ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የሲቪል ማኅበራት መሪዎችና ወጣቶች በአንድነት መክረዋል።