06/12/2025
የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ለሁሉም ህፃናት ተደራሽ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት ተገለፀ
ሀዋሳ: ሕዳር 26/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ለሁሉም ህፃናት ተደራሽ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያው 4ኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ላይ ለጤና ባለሙያዎች የአስልጣኞች ስልጠና በዞኑ ዋካ ከተማ ሰጥቷል ።
በስልጠናው ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ያዕቆብ ሌንጮ የፖሊዮ ክትባት ለሁሉም ህፃናት ማለትም ከአምስት አመት በታች የሚገኙ ህፃናት ቤት ለቤት በመጎበኝት መሰጠት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል ።
ስለሆነም በስልጠናው የተገኙ ባለሙያዎች ስልጠናውን በአትኩሮት ተከታትለው ለሌሎችም ሙያተኞች በተገቢ ሁኔታ እንደሚያሰለጥኑ እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋ ።
ስልጠናው የፖሊዮ ክትባት የተከተቡትም ያልተከተቡት ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህፃናት የመለየትና የመከታተል አገሎትም ተያይዞ እንደሚሰጥ የመምሪያው ሃላፊ ተናግረዋል ።
ስልጠናውን ከሰጡት አስልጣኞች መካከል በጤና መምሪያው ድንገተኛ አደጋ ቅኝት ምላሽ ዋና ስራ አስተባባሪ አቶ ወልዴ በካሎም በበኩላቸው በዞኑ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ቤት ለቤት መሰጠቱ በርካታ ጥቅም መኖሩን ተናግረው ለዚህም ተግባር ሙያተኞቹ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ሌሎቹን እንዲያሰለጥኑ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል ።
ስልጠናው ከፓሊዮ ክትባት በተጨማሪ የዞረ እግር፣ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ፣ የምግብ እጥረት ልየታ ፣ የአዲሱ ማርበርግ ቫይረስ ልየታና ህክምና አስጣጥ ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ለአሰልጣኞች በበቂ ሁኔታ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል ።
ከሰልጣኞቹ መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከመስጠታችን በፊት ስልጠና መስጠቱ የበለጠ ግንዛቤ እንደሚጨምር ተነጋግረዋል ።
የፖሊዮ ክትባትን ጨምሮ በሌሎችም በሽታዎች ዙሪያ ያገኘነውን ግንዛቤ ሌሎች ሙያተኞች በተገቢው ሁኔታ በመሰልጠን ወደ ተግባሩ እንደሚገቡም ተናግረዋል ።
ስልጠናው ከወረዳውና ከከተማ አስተዳደር የሚመለከታቸውን የዘርፉ ሙያተኞች ለተከታታይ ለሁለት ቀናት የተሰጠ ሲሆን፥ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከአምስት አመት በታች ለሚገኙ ህፃናት ከታህሳስ 3 እስከ 6/2018 ዓ/ም ድረስ ቤት ለቤት በሚደረግ ጎብኝት እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል ።
ዘገባው የደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ነው።