19/06/2025
የሠራተኞች መነሻ የደመወዝ ወለል 8,384 ብር እንዲሆን ተጠየቀ
* መንግሥት መነሻ ወለል ከ1,200 እስከ 2,000 ብር በሚል ረቂቅ አዋጅ አቅርቧል
* ከፍተኛ ግብር የሚጣልባቸው ሠራተኞች ደመወዝ ከ150,000 ብር ጀምሮ እንዲሆን አሳስቧል
ወርኃዊ ደመወዛቸው እስከ 8,384 ብር የሆነ ሠራተኞች ከግብር ነፃ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን ገለጸ፡፡ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለሪፖርተር እንዳሉት፣ ወርኃዊ ደመወዛቸው እስከ 8,384 ብር የሆነ ተቀጣሪ ሠራተኞች ከግብር ነፃ እንዲደረጉ ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በሥራ ላይ ቆይቷል የተባለውን የገቢ ግብር አዋጅ 979/2008ን ለማሻሻል ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከተባሉ ባለድርሻዎች ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ እስከ ሁለት ሺሕ ብር የሚከፈላቸው ሠራተኞች ከግብር ነፃ እንዲሆኑ ተደንግጓል፡፡
ኢሠማኮ እስከ 8,384 ብር ድረስ የሚከፈላቸው ተቀጣሪዎች ከግብር ነፃ እንዲሆኑ ለገንዘብ ሚኒስቴር በደብዳቤ እንደጠየቀ አስታውቋል፡፡ አቶ ካሳሁን በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት ዕለታዊ ገቢው ከሦስት ዶላር በታች የሆነ ሰው ደሃ በመሆኑ፣ የመንግሥት የገቢ ግብር በዚህ ወለል ሥር ያሉ ተቀጣሪዎችን ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
በማናቸውም ቀጣሪ ተቋማት የሚሠሩ ሠራተኞች በወር ከ8,384 ብር እስከ 22,974 ብር ደመወዝ የሚያገኙ ሠራተኞች፣ አሥር በመቶ ግብር እንዲጣልባቸው መንግሥትን መጠየቁን ኢሠማኮ ገልጿል፡፡
ከ22,975 እስከ 44,530 ብር ወርኃዊ ደመወዝ ተከፋዮች የ15 በመቶ፣ ከ44,531 እስከ 72,336 ብር የሚከፈላቸው ደግሞ 20 በመቶ፣ እንዲሁም ከ72,337 እስከ 107,449 ብር የ25 በመቶ ግብር እንዲጣልባቸው ኢሠማኮ በደብዳቤው አሳስቧል፡፡
ከ107,450 እስከ 150,107 ብር ድረስ የሚከፈላቸው ሠራተኞች 30 በመቶ ግብር፣ እንዲሁም 150,108 ብር እና ከዚያ በላይ የሚከፈላቸው ተቀጣሪ ሠራተኞች ደግሞ 35 በመቶ ግብር እንዲከፍሉ ለመንግሥት ባቀረበው ደብዳቤ ኢሠማኮ መጠየቁን ገልጿል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ባለው የሠራተኞች የገቢ ግብር አዋጅ መሠረት እስከ 600 ብር ድረስ የሚከፈላቸው ሠራተኞች ከግብር ነፃ ሲሆኑ፣ ከ10,900 ብር ጀምሮ ደግሞ 35 በመቶ ግብር እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ከአንድ ሳምንት በፊት ለውይይት ይፋ ባደረገው የገቢ ግብር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ 1,200 ብር፣ 1,600 ብር እና 2,000 ብር ወርኃዊ ደመወዝተኞች ከግብር ነፃ እንዲደረጉ ድንጋጌ መኖሩ ይታወሳል፡፡
የመንግሥት የገቢ ግብር ማሻሻያው ሠራተኞች ያለባቸውን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ታሳቢ ያላደረገ እንደሆነ የተለያዩ የውይይት ተሳታፊዎች አስተያየት መስጠታቸው አይዘነጋም።
(Ethiopian reporter )