30/06/2025
"ከእውነታው መሽሽ የህዝባችንን መከራ ያራዝማል እንጂ መዳኛችን ሊሆን አይችልም"
የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትን የህልዉና አደጋ ለመቀልበስ ያለ እረፍት በዱር በገደሉ እየደከሙ መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚገኙ አርበኞች የሞቱለት ዓላማ ዳር ሳይደርስ ትግላችን አደጋ ዉሰጥ መግባቱን በቀን 22 /2017 ዓ.ም አገዛዙ በጠራዉ ሰልፍ ላይ ተጨባጭና አመላካች ነገር ታዝበናል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ወጥና ውህድ ድርጅት በቀጠና ዕዝ ሰይሞ በመካከላችን የተፈጠረውን አለመግባባት እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወታደራዊ ስነ ምግባር በሌላቸው የፋኖ አባላትና አመራሮች ድርጊት ህዝባችን ከእጃችን እየወጣ ከአገዛዙ ጋር እንዲተባበር እና በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝቡ በጥሩምባ ሳይቀር እየተጠራራ የህዝባዊ ኃይሉ አመራር እና አባላት ጋር ወደ ግጭት ውስጥ እየገባ እንደሚገኝ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ትላንት በአማራ ክልል ላይ የተደረገው ሠልፍ ምንም እንኳ በአገዛዙ አስገዳጅነት ነው ሠልፍ የወጡት የሚሉ ተጠየቆችን ድርጅታችን (አፋብኃ) በጥልቀት የገመገመ ቢሆንም በዚህ ልክ አደባባይ ወጥቶ የድጋፍ ሠልፍ ያደረገን የህዝብ ማዕበል "ተገዶ ነው" የወጣው የሚለው ዉሃ የማያነሳ ምክንያት ነው።
የአማራ ህዝብ ወዶ እንጂ ተገዶ ለማያምንበት ዓላማ የማይሰለፍ ጀግና ህዝብ ነው። ከእውነታው መሽሽ የህዝባችንን መከራ ያራዝማል እንጂ ትክክለኛ መዳኛችን ሊሆን አይችልም። እውነታው በተደጋጋሚ በሠራናቸው ግፍና በደሎች ህዝቡ በእኛ ተስፋ እየቆረጠ ለአገዛዙ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑ መራራ እዉነት ነው።
ህዝብ ለምን ለአገዛዙ ድጋፍ ይሰጣል በሚል መነሻ ችግሩን ውጫዊ ማድረግ ሳይሆን ወደ ውስጣችን በጥልቀት በመመልከት ህዝብን በይፉ ይቅርታ በመጠየቅ ከዚህ በፊት ከህዝብ የነጠለንን ህዝብ ከሚያማርር ተግባር የአፋብኃ አባላት እና አመራሮች ራሳቸውን እንዲያርቁ እናሳስባለን። ይህ ትግል ብዙ ስኬቶችን ያስመዘገበ መሆኑ ባይካድም አመራሮቻችንና አባሎቻችን እንታገልለታለን ባልነው ህዝብ ላይ በሚፈጽሙት ግፍ ምክንያት የሕዝቡ ድጋፍ ከጋዜ ወደጊዜ እየቀነሰ ከመምጣቱም በላይ ምንም ሳይፈራ በመላው ክልል ከጎጥ እስከወረዳ የሰልፍ እንዳትወጣ ትዕዛዛችንን በመጣስ አገዛዙን ለመደገፍ ሰልፍ ወጥቷል። ይህ የህዝብ ማዕበል አገዛዙ በመቀስቀሱ ብቻ ሳይሆን በየአካባቢው ያለው ሀይላችን በሚያደርስበት በደል መማሩንና ሕዝብም ከጊዜ ወደ ጊዜ በጦር ሜዳው በምናጣው ድልና ልጆቹን ያለውጤት ማጣቱ አልበቃ ብሎ እያደረስንበት ያለውን ግፍና መከራ የገለጸበት ነው። በመሆኑም አፋብኃ ትግል ጎታች የሆኑ አመራሮቻችን ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ለህዝባችን የሚያሳውቅ መሆኑን ያሳስባል።
ጎጃም አማራ ፋኖ-Gojjam Amhara fano