20/06/2024
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ ቲክቶክ ላይ በሚለቃቸው ዳዕዋዎች የተነሳ ከሙስሊሙ አልፎ ብዙ የሌላ እምነት ተከታዮች የሚወዱት'ና የሚለውን የሚሰሙት ሰው ሆኗል።
ደግሞ ለሁሉም የሃይማኖት ተከታዬች የሚሆኑ መልዕክቶችን በሚያምር መልኩ ማስተላለፍ'ና መግለፅ በሚገባ ይችላል።
ከማስተማሩ በተጨማሪ ኡስታዝ መሬት ላይም የተለያዩ የበጎ ስራዎች በመስራት ይታወቃል። የሆነ ጊዜ ራሱ ኡስታዝ ኑሩ 'ሰዎችን ስንረዳ ተረጂዎችን በማያሸማቅ መልኩ መሆን አለበት...' ምናምን ሲል ሰምቼው ነበር። መልዕክቱም ለብዙ ሰዎች ተዳርሷል !
ታዲያ ይሄ መልዕክቶቹ በብዙዎች የሚሰማ ኡስታዝ ፣ ለሌሎች እንረዳለን ለሚሉ ሰዎችም አርአያ ሊሆን የሚገባው ሰው ለምን በዚህ ልክ ወርዶ ተረጂዎችን በሚያሸማቅ መልኩ ለአረፋ ስጋ ሲያከፋፍል ፎቶ መነሳት እንደፈለገ ሊገባኝ አልቻለም !? የዚህ አይነት ተረጂዎችን ክብራቸው'ና ማንነታቸውን በሚነካ መልኩ ፎቶ እያነሱ መርዳት እንኳን አንድ ኡስታዝ ላይ አይተን ማንኛውም ሰው ሲያረገው ልንቃወመው የሚገባ ነገር ነው !
ከታች ፎቶ ላይ አንድ የበሬ እግር ሲቀበል የምናየው ሰው እናት አባት ፣ ከዛም ሲያልፍ ሚስት'ና ልጆች ይኖሩታል። ዘመድ ጎረቤት አለው። ትላንት ኖሮት ዛሬ ያጣ ሰውም ሊሆን ይችላል። ታዲያ የዚህን ሰው ስጋ ሲቀበል የሚያሳይ ያዩ የቅርቡ ሰዎች ስለሚደርስባቸው ጫና እንዴት ኡስታዝ ኑሩ መረዳት ከበደው ? ሌሎች ህፃናትስ የዚህን ሰው ልጆች ለማብሸቅ ይሄ ፎቶ ቢጠቀሙበት ለሚደርስባቸው የስነልቦና ጉዳት ተጠያቂው ማን ነው ? አባታቸው ? ድህነታቸው ወይስ ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ ?
ሴቶቹም እንደዛው። የሚኖሩበት ሰፈር ድህነታቸው ፣ ማጣታቸው እንዳይታወቅ ቢሆንስ ወደዚህ የእርዳታ ድርጅት የመጡት ? በዚህ ልክ ክብራቸው ተቀምቶ የሚሰጣቸው አንድ'ና ሁለት ኪሎ ስጋ ሲያልቅ ይሄ ፎቶ ግን ለዘላለም አብሯቸው ይኖራል። ነገ ድህነትን ቢያመልጡ በዚህ ፎቶ የማይብሰለሰሉ'ና የማይቆጩ ይመስልሃል ?
ሁሌ እንደዚህ አይነት የሞራል ጥያቄ ሲነሳ 'ለሰጪዎቹ እርዳታው መድረሱን ለማሳየት ነው...' ምናምን የሚል የተለመደ መከላከያ አለ። ሰጪው የተገዙ በሬዎችን'ና ደረሰኝ ማየቱ በቂ ነው። ከዛ ባለፈ ባረደው በሬ ልክ 'የሰዎች ክብር አብሮ ሲገፈፍም በፎቶ ማየት እፈልጋለሁ...''ካለ ለእሱ ብቻ መላክ ይቻላል። ከዛ ባለፈ ግን እንደዚህ አይነት ፎቶ ፣ ሊያውም በዓል በደረሰ ቁጥር ለምሳ የሚሆን ስጋ እየሰጡ ተረጂዎችን ፎቶ ማንሳት ነውር ነው ! ይሄ ተግባር በአንድ የሃይማኖት አባት ሲደረግ ደግሞ ከነውርም ያልፋል ! ሌሎች ሰዎች 'እንኳን እኛ እነ ኡስታዝ እከሌስ ያደርጉት የለ እንዴ ?' ብለው የዚህ አይነት ተግባርን እንዲለማመዱት በር ይከፍታል !
(C) ሙስተጃብ ነኝ