29/04/2025
ረህማ ኢስላማዊ ድርጅት በንጽጽር ላይ ለሚሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅናና የምስጋና ሰርተፍኬት አበረከተ።
📌 በፕሮግራሙ ላይ ለኡስታዝ ሁሴን አህመድ (ሁሱ) የሽኝት ፕሮግራም ተደርጎለታል።
- ባሪክ ሚዲያ፥ ሚያዝያ 21/2017
ረህማ ኢስላማዊ ድርጅት በንጽጽር ዳዕዋ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ለሚገኙ ከ18 በላይ ለሆኑ ተቋማት እና ግለሰቦች የእውቅናና የምስጋና ሰርተፍኬት አበርክቷል።
በኤልጌል ሆቴል በተካሄደው የእውቅና ፕሮግራም ላይ በንጽጽር ዘርፍ የሚሰሩ ዳኢዎችን ጨምሮ ታላላቅ መሻይሆች ተገኝተው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሸይህ ሰኢድ አህመድ ሙስጠፋ በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ረህማ ኢስላማዊ ድርጅት ሙስሊም ላልሆኑ ግለሰቦች የኢስላምን ብርሀን ለማሳየት እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀው ሰዎች በግል ከመንቀሳቀስ ይልቅ ተቋምን ገንብተው የሚያደርጉት የዳዕዋ እንቅስቃሴ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣ ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ ላይ ራህማ ኢስላማዊ ድርጅት በከተማ ላይ ዳዕዋ፤ በትምህርት ቤት ዳዕዋና በገጠራማ ቦታዎች ላይ የሚያደርገውን የዳዕዋ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ዶክመንተሪ ቀርቧል።
ኡስታዝ ሁሴን አህመድ (ሁሱ) በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሰዎችን ወደ ኢስላም በመጣራት እያደረገ ላለው የዳዕዋ እንቅስቃሴ የምስጋና እውቅና ሰርተፍኬት እንዲሁም የሽኝት ፕሮግራም ተደርጎለታል።
በመጨረሻም ቢ ዌይ ቴክኖሎጂ በኢስላም ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾችን ያከተተ ሁሱ የተሰኘ ድረገጽ ለኡስታዝ ሁሴን አህመድ አበርክቷል።