20/08/2026
✞✞✞ እንኩዋን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ደብረ ታቦር በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
✞✞✞ ✞✞✞
=>ደብረ ታቦር በቁሙ እሥራኤል ውስጥ ከሚገኙ ተራሮች አንዱ ነው:: ተራራው ብዙ ታሪካዊ ዳራዎች ቢኖሩትም ክብሩ ከፍ ከፍ ያለው ግን ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ስለ ገለጸበት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
+አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደባት በዚያች በተወደደች ጊዜ: ደቀ መዛሙርቱ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ምሥጢርን ይማሩ ነበር:: በጊዜው ግን አበው ሐዋርያት ምሥጢር ባይገባቸው: አንድም ገና መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ አልወረደም ነበርና እምነታቸው ሙሉ አልነበረም::
+ጌታም አምላክነቱን በየጊዜው በቃልም: በተግባርም ይገልጥላቸው ነበር:: በርግጥ ያንን ነደ እሳት: ሰማያት የማይቸሉትን ግሩማዊ አምላክ በትሑት ሰብዕና መመልከቱ ሊከብድ እንደሚችል መገመት አያዳግትም::
+ጌታችን ብዙ ተአምራትን በአምላካዊ ጥበቡ ሠርቷል:: እጅግ ድንቅ ከሆኑት መካከል ደግሞ ቅድሚያውን ደብረ ታቦር ይይዛል:: ጌታ ስለ ምን መለኮታዊ ክብሩን በደብረ ታቦር ገለጸ ቢሉ:-
1.ትንቢቱ ሊፈጸም (መዝ. 88:12)
2.ምሳሌው ሊፈጸም (ባርቅና ዲቦራ በሢሣራ ላይ ድልን ተቀዳጅተዋልና)
3.ሊቀ ነቢያት ሙሴ "ልይህ" ብሎ ከ1,500 ዓመታት በፊት ጠይቆ ነበርና እርሱን ለመፈጸም
4.አንድነቱን: ሦስትነቱን ለመግለጽ
5.ቤተ ክርስቲያንን በምሳሌ ለማሳየት
6.ተራራውን ለመቀደስ
7.የሐዋርያቱን ልብ ለማጽናት . . . ወዘተ ነው::
+ነሐሴ 7 ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልዾስ ወስዶ "የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?" ብሎ ጠይቁዋቸው ነበር:: እነርሱም የራሳቸውን ሐሳብ የሌላ እያስመሰሉ "አንዳንዶቹ ኤልያስ: አንዳንዶቹም ሙሴ: ሌሎቹም ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል" አሉት::
+ኩላሊትን የሚመረምር ፈጣሪ ነውና "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ደንግጠው ዝም አሉ:: የሃይማኖት አባት: ባለ በጐ ሽምግልና ቅዱስ ዼጥሮስ ግን በመካከላቸው ቆሞ "አንተ ውዕቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው - የሕያው እግዚአብሔር አንድያ የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ አንተ ነህ" አለው:: በዚያን ጊዜ ቃለ-ብጽዓን እና የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ተሰጠው:: (ማቴ. 16:13)
+መጽሐፍ እንደሚል ደግሞ እንዲህ ከሆነ ከ6ኛው ቀን በሁዋላ ጌታችን 12ቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ደብረ ታቦር ወሰዳቸው:: ዘጠኙን በእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ 3ቱን (ዼጥሮስን: ዮሐንስንና ያዕቆብን) ይዟቸው ወጣ:: እኒሕ ሐዋርያት "አዕማድ: አርዕስት: ሐዋርያተ ምሥጢርም" ይባላሉ::
+በተራራው ላይ ሳሉም ድንገት የጌታችን መልኩ ከፀሐይ 7 እጅ አበራ: ከመብረቅም 7 እጅ አበረቀ:: "ወኮነ ልብሱ ጸዐዳ ከመ በረድ" እንዲል ከታቦር የተነሳው ብርሃነ ገጹ አርሞንኤም ደርሷል:: ያንን ተመልክተው መቆም ያልቻሉት ሐዋርያቱ ፈጥነው መሬት ላይ እንደ ሻሽ ተነጠፉ::
+በዚያች ሰዓት ሙሴ ከመቃብር: ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን መጡ:: አንዳንዶቹ ጌታን 'ነቢይ' (ሎቱ ስብሐት) ብለውታልና ሙሴና ኤልያስ ተናገሩ:- "ስለ ምን አንተን ነቢይ ይሉሃል: እግዚአ ነቢያት - የነቢያት ፈጣሪ ነህ እንጂ" እያሉ ተገዙለት: አመሰገኑት::
+ነገር ግን በቦታው ጸንተው መቆየት አልቻሉም:: መለኮታዊ ብርሃኑ ቢበዘብዛቸው ቅዱስ ሙሴም ወደ መቃብሩ: ቅዱስ ኤልያስም ወደ ማደሪያው በድንጋጤ ሩጠዋል::
+በዚያች ሰዓት ሊቀ ሐዋርያት ጌታን "ሠናይ ለነ ኀልዎ ዝየ: ንግበር ሠለስተ ማሕደረ: አሐደ ለከ: ወአሐደ ለሙሴ: ወአሐደ ለኤልያስ - ጌታ ሆይ! በዚህ መኖር ለኛ መልካም ነው:: በዚህም 3 ዳስ እንሥራ:: አንዱን ላንተ: አንዱንም ለሙሴ: አንዱን ለኤልያስ" ብሎታል::
+ቅዱስ ዼጥሮስ ለራሱ ሳያስብ ለጌታና ለቅዱሳን ነቢያቱ "ቤት እንሥራ" በማለቱ ሲመሰገን ጌታን የመጣበትን የማዳን ሥራ የሚያስተው ጥያቄ በማቅረቡ ከድካም ተቆጥሮበታል:: ለሁሉም ግን ሐሳቡ ድንቅና መንፈሳዊ ነው::
+እርሱ ይሕንን ሲናገር መንፈስ ቅዱስ በደመና አምሳል ወረደና ከበባቸው:: አብ ከሰማይ ሆኖ "ዝንቱ ውዕቱ ወልድየ ዘአፈቅር: ወሎቱ ስምዕዎ - የምወደው: የምወልደው: ሕልው ሆኘ የምመለክበት የባሕርይ ልጄ እርሱ ነውና ስሙት" ሲል ተናገረ::
+ደቀ መዛሙርቱም ከፍርሃት የተነሳ በዚያች ሰዓት እንደ በድን ሁነው ነበርና ጌታችን ቀርቦ ቀሰቀሳቸው:: በተነሱ ጊዜ ግን ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ተመልሶ ነበር:: (ማቴ. ማር. ሉቃ. )
+በደብረ ታቦር የጌታችን ብርሃነ መለኮት ያዩ 3ቱ ሐዋርያት ብቻ አይደሉም:: እመ ብርሃን ካለችበት ሆና ስትመለከት 12ቱ ሐዋርያት ደግሞ በተራራው ሥር ሆነው በተደሞ ተመልክተዋል::
+ይሕንን ድንቅ ብርሃነ መለኮት ያላየ ይሁዳ ብቻ ሲሆን እርሱም ስለ ክፋቱ የኢሳይያስ ትንቢት ተፈጽሞበታል:: ኃጢአተኛው የእግዚአብሔርን ክብር እንደማያይ ተነግሮበታልና:: "ያአትትዎ ለኃጥእ ከመ ኢይርዐይ ስብሐተ እግዚአብሔር" እንዲል:: (ኢሳ.)
ሊቁም የደብረ ታቦርን ምሥጢር ሲያደንቅ እንዲህ ብሏል:-
"ጸርሐ አብ ኪያከ በውዳሴ:
ወበርእስከ ጸለለ መንፈሰ ቅዳሴ:
አመ ገበርከ እግዚኦ በታቦር ምስለ ሐዋርያት ክናሴ:
መንገለ ሀሎ ኤልያስ ወኀበ ሐለወ ሙሴ:
ዘመለኮትከ ወልድ ከሠትከ ሥላሴ::"
=>ለወዳጆቹ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠ ጌታ የእኛንም ዐይነ ልቡናችንን ያብራልን:: ከበዓሉ በረከትም ያሳትፈን::