27/07/2025
የጥቅል ጎመን 8 አስደናቂ የጤና ጥቅሞች
ጥቅል ጎመን በቀላሉ የማይገመት የጤና በረከት ያለው አትክልት ነው። የአጥንትና የልብ ጤናን ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ ጥቅሞች አሉት።
በውስጡ በሚገኘው ፋይበር (fiber)፣ ቫይታሚን ሲ እና ቫይታሚን ኬ ምክንያት ለጤናችን ተመራጭ ያደርገዋል።
በተጨማሪም ካሎሪው በጣም ዝቅተኛ ነው፤ አንድ ኩባያ የተከተፈ ጥሬ ጥቅል ጎመን 17.5 ካሎሪ ብቻ ይይዛል።
ጥቅል ጎመን መነሻው ከአውሮፓ ሲሆን፤ በጥሬውም ሆነ አብስለን መመገብ እንችላለን።
ጠቃሚ ምክር
ሁሉንም ወይም ሙሉ ጥቅሞቹን ለማግኘት፣ አብስሎ ከመመገብ ይልቅ በጥሬው ሰላጣ ሠርቶ መመገብ ወይም ለትንሽ ጊዜ በዘይት ጠብሶ መጠቀም ይመከራል። ለረጅም ጊዜ ሲበስል አንዳንድ ንጥረ ነገሮቹን ሊያጣ ይችላል።
የጥቅል ጎመን የጤና ጥቅሞች
1.ዋጋው ተመጣጣኝ እና ዝቅተኛ ካሎሪ ስላለው
ክብደት ለመቀነስ እየሞከሩ ከሆነ፤ ከፍተኛ የካሎሪ ይዘት ያላቸውን ምግቦች ዝቅተኛ ካሎሪ ባላቸው መተካት ተገቢ ነው።
አንድ ኩባያ የተከተፈ ጥሬ ጎመን 17.5 ካሎሪ ብቻ ስላለው ክብደትን ለመቆጣጠር ወይም ለመቀነስ ተመራጭ ያደርገዋል።
ብዙ ንጥረ ነገር ያላቸው ምግቦች ውድ ሲሆኑ፤ ጥቅል ጎመን ግን በዋጋው በጣም ተመጣጣኝ ነው።
2.የደም ግፊትን ለመቆጣጠር ይረዳል
በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች ለልብ ህመም እና ለስትሮክ (ለአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ) የሚያጋልጥ ከፍተኛ የደም ግፊት ችግር አለባቸው።
ጥቅል ጎመን የደም ግፊትን ለመቆጣጠር የሚረዳውን ፖታሺየም በውስጡ ይዟል። ፖታሺየም የነርቭ እና የጡንቻን ሥራ የሚያግዝ፣ እንዲሁም የልብ ምትን የሚያስተካክል ንጥረ ነገር ነው።
በሰውነታችን ውስጥ የሶዲየም (ጨው) መጠን ሲበዛ የደም ግፊት ስለሚያስከትል፤ ፖታሺየም ይህንን የጨው ተጽዕኖ ለመቀነስ ይረዳል።
3.የካንሰር ሴሎች እድገትን ሊከላከል ይችላል
እንደ ጥቅል ጎመን ያሉ አትክልቶች ግሉኮሲኖሌትስ (glucosinolates) የተባሉ ንጥረ ነገሮችን ይይዛሉ።እነዚህ ሰልፈር ያላቸው ኬሚካሎች ለጥቅል ጎመን መራራ ጣዕም ተጠያቂ ወይም መንስእኤዎች ናቸው።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ሰውነታችን እነዚህን ንጥረ ነገሮች ወደ ካንሰር ተከላካይነት ባህሪ ወዳላቸው ውህዶች ይለውጣቸዋል።
ይህ ማለት ግን ጥቅል ጎመን መመገብ ካንሰርን ሙሉ በሙሉ ይከላከላል ማለት አይደለም፤ ተጨማሪ ምርምር ቢያስፈልግም፥ ጥቅል ጎመንን በአመጋገብ ውስጥ ማካተት ጤናማ ምርጫ ነው።
4.የአጥንት ጤናን ሊያሻሽል ይችላል
ጥቅል ጎመን ለአጥንት ጤና እና ለደም መርጋት ወሳኝ የሆነውን ቫይታሚን ኬ በውስጡ ይዟል።
አንድ ኩባያ ጥሬ ጥቅል ጎመን 53 ማይክሮግራም ቫይታሚን ኬ ሲይዝ፤ ወንዶች በቀን 120 እንዲሁም ሴቶች 90 ማይክሮግራም ያስፈልጋቸዋል።
የቫይታሚን ኬ እጥረት ኦስቲዮፖሮሲስ (የአጥንት መሳሳት) እና ለደም መፍሰስ ችግር ሊያጋልጥ ይችላል።
5.ከልብ ሕመም ይከላከላል
ጥቅል ጎመን ለልብ ጤና ጠቃሚ መሆኑን ላያስቡ ይችላሉ፤ ነገር ግን በአመጋገብዎ ውስጥ ቢጨምሩት ይመረጣል።
በውስጡ ያሉት ንጥረ ነገሮች በሰውነት ውስጥ እብጠትን በመቀነስ ለልብ ህመም ያለውን ተጋላጭነት እንደሚቀንሱ ጥናቶች ያሳያሉ።
አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ ብዙ ጥቅል ጎመን የሚመገቡ ሴቶች ለልብ ህመም ተጋላጭነትን ሊያመለክት ከሚችል የደም ቧንቧ መጥበብ (AAC) በ46% ያነሰ ተጋላጭ ነበሩ።
6.ኢንፍላሜሽንን (እብጠትን) ይቀንሳል
የረጅም ጊዜ ኢንፍላሜሽን (Chronic inflammation) በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ሴሎችን ሊጎዳና እንደ አርትራይተስ (የቁርጥማት በሽታ)፣ ካንሰር፣ የስኳር በሽታ እና የልብ ህመም ላሉ በሽታዎች ተጋላጭነትን ይጨምራል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ እንደ ጥቅል ጎመን ያሉ አትክልቶችን መመገብ በሰውነት ውስጥ ያሉ የእብጠት ወይም የኢንፍላሜሽን ምልክቶችን ይቀንሳል።
7.በቫይታሚን ሲ የበለፀገ ነው
ሰውነታችን ቫይታሚን ሲን በራሱ ስለማያመርት ከምግብ ማግኘት አስፈላጊ ነው። ጥቅል ጎመን ደገሞ ጥሩ የቫይታሚን ሲ ምንጭ ነው።
ቫይታሚን ሲ ሰውነታችን ከአትክልት የምናገኘውን አይረን (ብረት) እንዲመጥ፣ ቁስል እንዲድን፣ እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም እንዲደግፍ ይረዳል።
8.ለምግብ መፈጨት ሥርዓት ጠቃሚ ነው
ጥቅል ጎመን በፋይበር (fiber) የበለጸገ በመሆኑ ለምግብ መፈጨት ሥርዓት በጣም ጠቃሚ ነው።
ፋይበር ለረጅም ሰዓት የጥጋብ ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል፣ የሆድ ድርቀትን ያስታግሳል፣ በደም ውስጥ ያለን የስኳር መጠን ይቆጣጠራል፣ እንዲሁም አጠቃላይ የኮሌስትሮል መጠንን ለመቀነስ ይረዳል።
-የጥቅል ጎመን የንጥረ-ምግብ ይዘት
የጥቅል ጎመን የንጥረ-ምግብ ይዘት (በአንድ ኩባያ የተከተፈ ጥሬ ጥቅል ጎመን ውስጥ):-
ካሎሪ:- 17.5
ስብ (ፋት):- 0.1 ግራም
ካርቦሃይድሬት:- 4.1 ግራም
ፋይበር:- 1.8 ግራም
ፕሮቲን:- 0.9 ግራም
ጥቅል ጎመን በአጠቃላይ ደህንነቱ የተጠበቀ ቢሆንም፤ አንዳንድ ሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።
የደም መርጋት የሚከላከሉ መድኃኒቶች (ለምሳሌ እንደ ዋርፋሪን ያሉ):- የሚወስዱ ከሆነ በጥቅል ጎመን ውስጥ ያለው ቫይታሚን ኬ ከመድኃኒቱ ጋር መስተጋብር ወይም ግጭት ሊፈጥር ስለሚችል ሐኪምዎን ያማክሩ።
የምግብ መፈጨት ችግር:- ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመገቡ በውስጡ ባለው ከፍተኛ ፋይበር ምክንያት የሆድ መነፋትና ጋዝ ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ ቀስ በቀስ በምግብ ገበታዎ ውስጥ ማካተት ይመከራል።
የአለርጂ ችግር:- አልፎ አልፎ ለአንዳንዶች የአለርጂ ምላሽ ሊያስከትል ይችላል።
(Ethio Tena)