
17/08/2025
ዜሌንስኪ ሩሲያ ጦርነቱ እንዳያበቃ 'እያወሳሰበች' ነው አሉ
| የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነቱን አለመቀበሏ ጦርነቱን ለማቆም የሚደረገውን ጥረት እያወሳሰበ ነው አሉ።
ፕሬዚዳንቱ በኤክስ ገጻቸው ላይ ላይ በለጠፉት ጽሑፍ "ሩሲያ በርካታ የተኩስ አቁም ጥሪዎችን ውድቅ ስታደርግ እና ግድያውን መቼ እንደምታቆም ገና አለመወሰኗን ተመልክተናል።ይህ ሁኔታውን ያወሳስበዋል" ብለዋል።
ዜሌንስኪ ሰኞ ዕለት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ተጉዘው የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት የሚያገኙ ሲሆን፣ትራምፕ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱን እንዲቀበል እጠይቀዋለሁ ብለዋል።
ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከተገናኙ በኋላ በዩክሬን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚለውን ሃሳባቸውን በመተው፣ ዘላቂ የሰላም ስምምነት ለማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ የአቋም ለውጥ በማድረግ አርብ የተካሄደውን የመሪዎች ስብሰባ ተከትሎ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ "በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን አሰቃቂ ጦርነት ለማስቆም ምርጡ መንገድ ነው" ብለዋል። የተኩስ አቁም ስምምነትን ብዙ ጊዜ "አይዘልቅም" ሲሉም ተችተዋል።
ከጉባኤው በኋላ ከትራምፕ ጋር በስልክ ውይይት ያደረጉት ዜሌንስኪ እውነተኛና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ በማቅረብ "ተኩሱ መቆም" እንዲሁም ግድያ ማብቃት አለበት ብለዋል።
ዜሌንስኪ ይህንን ካሉ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሰጡት መግለጫ ከሞስኮ ጋር "እውነተኛ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም" ለማግኘት አስፈላጊ ያሏቸውን መስፈርቶች አስፍረዋል።
በተጨማሪም "አስተማማኝ የሆነ የደህንነት ዋስትና" እና በክሬምሊን "ከተያዙ ግዛቶች ታፍነዋል" ያሏቸውን ሕጻናት እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
የትራምፕ አስተያየት የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት እንዲቆም ያላቸው አቋም ላይ ሙሉ በሙሉ ለውጥ ማድረጋቸውን የሚያሳይ ሲሆን፣ አርብ ዕለት ፑቲንን ከማግኘታቸው በፊት "በፍጥነት" የተኩስ አቁም እንዲደረግ እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።
የዩክሬን ዋና ፍላጎት ስለረዥም ጊዜ ስምምነት ከመነጋገር በፊት አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ሲሆን ትራምፕ ለአውሮፓ መሪዎች ስለ ስብሰባው ዓላማ ሲያስረዱ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሆነ መናገራቸው ተዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፑቲን ዩክሬን የዶኔትስክ ግዛት አካል ከሆነችው ዶንባስ እንድትወጣ የሚጠይቅ የሰላም ስምምነት ለትራምፕ አቅርበው ነበር ተብሏል።
በምላሹም ሩሲያ በዛፖሪዝህዚሂያ እና ኬርሰን ባሉት አካባቢዎች ወታደሮቿ ባሉበት እንዲቆሙ ለማድረግ አማራጭ ሃሳብ አቅርባለች።
ሩሲያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 2014 ክሬሚያን ከዩክሬን በሕገ ወጥ መንገድ ከወሰደች ከስምንት ዓመታት በኋላ በአገሪቱ ላይ ሙሉ ወረራ ፈጽማለች።
ከወረራው በኋላም ዶንባስን እና አብዛኛውን ሉሃንስክን እንዲሁም 70 በመቶ የሚሆነውን የዶኔትስክን ግዛት ተቆጣጥራለች።
ከዚህ ቀደም የትኛውም የሰላም ስምምነት "አንዳንድ የግዛቶች መለዋወጥን ያካትታል" ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ከጉባኤው በኋላ ለዜሌንስኪ ይህንኑ አቋማቸውን አቅርበዋል ተብሏል።
ከቀናት በፊት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ሩሲያ የሉሃንስክ እና የዶኔትስክ ክልሎችን ያቀፈውን ዶንባስን እንድትቆጣጣር እንደማይፈቅዱ ገልፀው፣ ወደፊት ለምትሰነዝራቸው ጥቃቶች እንደ መንደርደሪያ ሊያገለግሉ ይችላሉ ማለታቸው ይታወሳል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ትራምፕ ሰኞ ዕለት ዜሌንስኪን ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ጋር ተወያይተውባቸው ሊሆን የሚችሉ ጉዳዮች ላይ እንዲስማሙ ግፊት ሊያደርጉ ይችላሉ።
ሲቢኤስ ምንጮችን ጠቅሶ ትራምፕ ከጉባኤው በኋላ ለአውሮፓ መሪዎች በስልክ እንደተናገሩት ፑቲን "አንዳንድ ለውጦችን" እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ነገር ግን ምን እንደሆኑ ሳይገልጹ መቅረታቸውን ዘግቧል።
አርብ የተካሄደውን የመሪዎች ጉባኤ ተከትሎ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ትራምፕ ለዩክሬኑ መሪ ምን ዓይነት ምክር እንደሚሰጡ ተጠይቀው "ተስማማ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለውም "ሩሲያ በጣም ትልቅ ኃይል አገር ናት እና እነሱ ግን አይደሉም" ብለዋል።
ትራምፕ ቀደም ሲል ፑቲን ጦርነቱን ለማቆም የማይስማማኡ ከሆነ "በጣም ከባድ ቅጣት" እንደሚጠብቃቸው ዝተው ነበር።
ባለፈው ወር ሞስኮ የተኩስ አቁም ላይ እንድትደርስ አለበለዚያ ግን ሁለተኛ ደረጃ ታሪፎችን ጨምሮ ከባድ አዲስ ማዕቀቦች እንደሚጣሉባት በማስጠንቀቅ ቀነ ገደብ አስቀምጠው ነበር።
አርብ የተካሄደውን የመሪዎች ጉባኤ ተከትሎ ሁለቱም ፕሬዚዳንቶች ስለተደረሰው ስምምነት የተገለፀ ነገር የሌለ ሲሆን ትራምፕ ግን ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።
ቅዳሜ ዕለት ፑቲን ስብሰባውን "በጣም ጠቃሚ" ሲሉ የገለፁት ሲሆን፣ ለትራምፕ "አቋማችንን ማሳወቅ ችለናል" ብለዋል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት "የቀውሱን መነሻ፣ ስለ አጀማመሩ ለማስረዳት ዕድል ነበረን፤ እርሱን ነው ያደረግነው። የመግባባያችን መሰረት መሆን ያለበት እነዚህን ዋነኛ ምክንያቶች ማስወገድ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ ከፍተኛ የሩሲያ ዲፕሎማት ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአላስካ የተካሄደው የመሪዎች ስብሰባ ጦርነቱን ለማቆም "ለተጨማሪ ጥረቶች በጣም ጠቃሚ እርምጃ ነው።"
በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያ የመጀመሪያ ምክትል ቋሚ ተወካይ ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ እንዳሉት ሰላምን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው "በውጤቱ ሊረካ ይገባል።"
ፑቲን ከዜለንስኪ ጋር ይገናኙ እንደሆነ ግን ያሉት ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፈረንሳይን እና ጀርመንን ጨምሮ ለዩክሬን ድጋፋቸውን ለማጠናከር ቃል የገቡ እና "የፈቃደኞች ጥምረት" በመባል የሚታወቁት አገራት ዜሌንስኪ ወደ ዋይት ሐውስ ከመሄዳቸው በፊት እሁድ ከሰዓት በስልክ ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፣የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ ሜርዝ እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየንን ጨምሮ የአውሮፓ መሪዎች ቡድን "የሚቀጥለው እርምጃ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪን ያካተተ ተጨማሪ ውይይት መሆን አለበት" ብለዋል።
መሪዎቹ በአውሮፓ ድጋፍ የሦስትዮሽ ጉባኤ እንዲካሄድ "ለመሰራት ዝግጁ" መሆናቸውን ተናግረዋል ።
አክለውም "በሩሲያ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመደገፍ ዝግጁ ነን" ያሉ ሲሆን "ስለ ግዛቶቿ መወሰን የዩክሬን ጉዳይ ነው። ዓለም አቀፍ ድንበሮች በኃይል መለወጥ የለባቸውም" ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ትራምፕ ጦርነቱን ለማቆም ያደረጉትን ጥረት አድንቀው "ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አቀራርቦናል" ብለዋል።
"ለውጥ ቢኖርም ቀጣዩ እርምጃ ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ያካተተ ውይይት መሆን አለበት። በዩክሬን የሚኖር ሰላም ያለእርሱ ተሳትፎ ሊወሰን አይችልም" ብለዋል።
Via :- VOA
Like & Share ~> The Ethiopian
Tiktok:- https://www.tiktok.com/
Instagram :- https://www.instagram.com/theethiopian9
Youtube :- https://www.youtube.com/
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት ፎለው (Follow) ያድርጉ :: እናመሰግናለን !!!